የሀገር ውስጥ ዜና

ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች አሰቃቂ ወንጀሎች መፈጸሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ

By Feven Bishaw

October 29, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች እና ሰብዓዊ ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ዜጎች አሰቃቂ ወንጀሎች መፈጸሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተጠቀሱት አካባቢዎች የተፈጸመውን ወንጀል ምርመራን እና የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት ውጤቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

 

አንድን ሴት እስከ 15 በመሆን እየተፈራረቁ መድፈር፣ እናት እና ልጅን በአንድ ላይ መድፈር፣ ከተፈጥሮ ተቃራኒ የወሲብ ጥቃቶችን መፈፀም፣ ልጆችን በእናቶቻቸው ፊት መድፈር፤ ከደፈሩ በኋላ በጠመንጃ አፈሙዝ ብልቷን በመውጋት የፌስቱላ ተጠቂ እንድትሆን ማድረግ፣ የ8 ወር መጫትን ጨቅላ ልጇን በፈላ ውሃ ውስጥ እንጨምራለን በማለት እናትዋን በማስፈራራት መድፈር ይገኝበታል፡፡

እንዲሁም አንዲት የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሴትን ለሶስት አስገድዶ መድፈር፣ የመደፈር ወንጀል የደረሰባቸው ሴቶች ለአባላዘር እና ለአእምሮ ጤና መታወክ በሽታዎች ተጋላጭ ማድረግ፣ የተለየ የስነ ልቦና ጫና ለማድረስ በሚል የማህበረሰቡ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች የሆኑትን የካህናት ሚስቶችን እና ቆራቢ መነኮሳትን ለይቶ አስገድዶ መድፈር፣ በአፋር ክልል ሴቶችን ለረዥም ጊዜ አግቶ በማቆየት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በተደጋጋሚ በመፈጸም እና የህክምና እርዳታም ሳያገኙ አቆይተው መልቀቀ ናቸው።

በተጨማሪም ደባርቅ ወረዳ አብርሃም ቀበሌ ሟች ዘለቀ አስመራ የተባለ አባትን ከህጻን ልጁ ፊት አንገቱን በማረድ ሶስት ልጆቹ እግሩን እና እጁን እዲይዙ በማድረግ ከአንገቱ እስከ ሆዱ በልጆቹ ፊት በሳንጃ አካሉን መሰንጠቅ፣ የማህበረሰቡ መኖሪያ ቤቶችን የሞቱ የሽብር ቡድኑ አባላትን ለመቅበሪያነት እና ለመጸዳጃ ቤት ለምግብ ማብሰያነት መጠቀም፣ እንዲሁም ቤቶችን በማፍረስ፣ ሰዎችን በማገት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም።

በመንግስት የጤና ተቋማትን መዝረፍ እና ሙሉ በሙሉ በማውድም ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ በወንጀሉ የአስገድዶ መድፈር እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግ፣ ማህበራዊ አገልገሎት የሚሰጡ ባንኮችን፣የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ፣ የመብራት ኃይል አውታሮች ላይ ዘረፋ እና ጉዳት ማድረስ።

በአፋር ክልል የስድስት ወር ህጻን የእናቱን ጡት እንደያዘ በከባድ መሳሪያ ከእነ እናቱ ተመትቶ ተገድሏል።