በአማራ ክልል በተመረጡ 61 ትምህርት ቤቶች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተመረጡ 44 የ1ኛና በ17 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የሙከራ ትግበራው በህዳር 2014 ዓ.ም እንደሚጀምር የቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶቹ በሚጀመረው አዲስ ስርአተ ትምህርት ከ77 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።
በትምህርት ቤቶቹ አዲሱን ስርአተ ትምህርት ለመጀመር አጋዥ የመማሪያና ማስተማሪያ መፃህፍት ዝግጅት ተጠናቆ የህትመት ስራ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
የመማር ማስተማሩን ስራ ለሚያከናውኑ 1 ሺህ 639 መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
“በሙከራ ትግበራው ወቅት የሚታዩ ችግሮችን ለይቶ በማስተካከል በቀጣይ አመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል” ብለዋል።
ቀደም ሲል የነበረው ስርዓተ ትምህርት መልካም ሰብዕናን መቅረፅ የማያስችል እንደነበር አስታውሰው፤ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተማሪዎችን መልካም ስብዕናን መገንባት የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በክልሉ ተማሪዎች ከዕድሜያቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ዕውቀትና ክህሎትን እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ትምህርት ቤቶችን እንደገና የማደራጀት ተግባር ይካሄዳል።
“አዲሱ ስርአተ ትምህርት እንደየ ትምህርት አይነቱ ሀገር በቀል ዕውቀትን አካትቶ የተቀረጸና ህፃናት በመልካም ስነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ የሚያስችል ነው” ያሉት ደግሞ በስርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ የተሳተፉት የቋንቋና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው ናቸው።
ስርአተ ትምህርቱ ተማሪዎች ባህላዊ እሴቶችን በአግባቡ አውቀው እንዲያድጉና እንዲያጎለብቱ በማድረግ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የስራና ክህሎት ትምህርት በተጨማሪነት በስርዓተ ትምህርቱ እንዲካተቱ ተደርገዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ቀደም ሲል የታዩ ችግሮች እንዳይደገሙ በየደረጃው የሚገኙ መምህራን በዝግጅት ሂደቱ ወቅት እንዲሳተፉ መደረጉን ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!