Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ቁርጠኛ ናት – አምባሳደር ጊታ ፓሲ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ጠንካራ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ አስታወቁ።

በአምባሳደሯ የተመራ ሉዑክ ዛሬ የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጎብኝቷል።

አምባሳደሯ ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በአፍሪካ በጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በመንግስት የተገነባ የመጀመሪያ ፓርክ መሆኑን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

በፓርኩ የአሜሪካው “ፒ. ቪ. ኤች “ካምፓኒን ጨምሮ በርካታ አምራች ኩባንያዎች ያሉበት እንደሆነም መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በፓርኩ ውስጥ በርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን በመመልከታቸው መደሰታቸውን የገለጹት አምባሳደሯ፣ ከእነዚህ ሴቶች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

ስራቸውን ተረጋግተው ማከናወን እንዲችሉ በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት በኩል እንዴት ልረዳቸው እንችላለን በሚሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ አሜሪካ ከሰሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የፈቀደችው ምርታቸውን ከቀረጥና ኮታ ነጻ ወደአሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚረዳው የ”አጎዋ” ስምምነት በሠራተኞቹ ህይወት ላይ ስላለው በጎ አስተዋጽኦ ከጉብኝቱ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

“የፓርኩ ሠራተኞች በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ደስተኛ መሆናቸውን መስማት ያስደስታል” ያሉት አምባሳደሯ፣ በሰራተኞቹ ህይወት ላይ የተፈጠረውን ለውጥ ማጠናከር ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታም የተማሪዎችን የሠላም ክበብ የጎበኙ ሲሆን ተማሪዎች የእርስ በርስ ግንኙነትና ሰላምን ለማጠናከር እያደረጉት ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራቸው አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ጠንካራ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቁርጠኛ መሆኗን ነው በመግለጫቸው ያስታወቁት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.