በጎንደር ከተማ ከ480 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ተጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጎበኙ፡፡
የልማት ፕሮጀክቶቹ በከተማው የሚገኙ ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
የአስተዳደሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ አንዱአለም ሙሉ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ፤እየተገነቡ ያሉት የልማት ፕሮጀክቶች 112 ናቸው፡፡
ከልማት ፕሮጀክቶቹ መካከል የውስጥ ለውስጥ የጠጠርና የ16 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች እንዲሁም ስምንት አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ ድልድዮች ይገኙባቸዋል፡፡
የወጣቶች መዝናኛ ማልዕከላት፣ የጎርፍ መፋሰሻ ቦዮች፣ የአረንጓዴ ፓርኮችና መናፈሻዎች የመንገድ ዳር መብራቶች ዝርጋታ ስራዎች እንዳሉበትም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡
የልማት ፕሮጀክቶቹ የሚከናወኑት ከዓለም ባንክ፤ ከከተማ አስተዳዳሩና ከክልል የመቀናጆ ፕሮጀክት በተመደበ በጀት እንደሆነ ነው ያመለከቱት።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ጸጋው እዘዘው ፤ ምክር ቤቱ ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተሰርተው መጠናቀቀቸውንና የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ይቆጣጠራል ብለዋል፡፡
በከተማው በአንዳንድ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት መጓደልና የተቋራጮች አቅም ማነስ እንዲሁም የግንባታ መጓተቶች እንደሚስተዋሉ አንሰተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በየጊዜው በሚያካሂደው የመስክ ምልከታ የማስተካከያና የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለህዝብ ጥቅም እንዲውሉ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመሰረተ ልማት ጉብኝቱ የምክር ቤቱ አባላት፣የከተማው አስተዳደር አመራሮችና የልማት ፕሮጀክቶቹ ተቋራጮች ተሳታፊ መሆናቸውን ነው ኢዜአ የዘገበው፡፡