Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቅለው በባህርዳር ከተማ ዘንዘልማ ቀበሌ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመተውን የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሲሆኑ፥ አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ያደረሰው ግፍና በደል በመላ ኢትዮጵያ የደረሰ ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ አሸባሪ ቡድኑን መላ ኢትዮጵያውያን ተረባርበው በመቅበር ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ እና ማቋቋም እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ዛሬ የተደረገው ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የምግብና የአልባሳት ድጋፍም ከተማ አስተዳደሩ ከተፈናቃዮች ጎን መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ አብራርተዋል።
ከንቲባ አዳነች ተፈናቃዮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዛሬ በጊዜያዊ መጠለያ ብትኖሩም ከድል በኋላ ወደ ቀያችሁ እንደምትመለሱ አንጠራጠርም ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ሥራም እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ፥አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ በፊት በሽብር ቡድኑ ከተፈናቀሉ ወገኖች ጎን በመሆን አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል።

 ዛሬም ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና  በማቅረብ፥ ክልሉ ከሁሉም የጸጥታ ኀይሎችና ከሕዝቡ ጋር በመሆን አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽብርተኛውን ቡድን ለመደምሰስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ አሚኮ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.