ሽብርተኛውን የትህነግ ቡድን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል – ብልፅግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የወቅቱ የጋራ ጠላታችን ለሆነው ትህነግ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ከንቱ ምኞቱን በሚገባው ቋንቋ አስረድተን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል ሲል ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ በማህበራዊ የትስሰር ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፍ እንደገለጸው፥ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በቅጥፈት እጆቹ ጠፍጥፎ የጋገራት ህብስት አድርጎ በመቁጠር እሱ ባሻው ሰዓት የሚያቦካትና የሚፈረካክሳት ጡብ አድርጎ ይቆጥራታል።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያንን በጎሣ እና በመንደር በመከፋፈል፥ ኢትዮጵያ ሕልውናዋን መቼም ልታጣ አትችልም ሲል በአጽንኦት ገልጿል።
ኢትዮጵያዊነት የሕብር መገለጫ፣ የዜግነት ክብር እና ኢትዮጵያዊ በመሆን ብቻ የሚገነዘቡት እውነት እንጂ አየር ላይ የተበተነ ጉም አይደለም ሲልም ነው ያብራራው፡፡
አያይዞም ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን በአገሪቱ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ መከራ ሲዘራና ሲያሳጭድ መቆየቱን የጠቀሰው ብልጽግና ፓርቲ፥ ነፃ አወጣዋለሁ የሚለውንም የትግራይ ህዝብ በነፃ አውጪ ስም በርካታ ግፍና መከራ ሲያሸክመው መኖሩን አስረድቷል።
አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣አጥንታቸውን ከስክሰው ከወራሪ ጠላት ጠብቀው ያስረከቡንን ውድ አገራችንን፥ የወቅቱ የጋራ ጠላታችን የሆነው ትህነግ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ከንቱ ምኞቱን በሚገባው ቋንቋ አስረድተን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል ብሏል ፓርቲው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን በማንኳሰስ የሚለወጥ አንዳች ነገር እንደሌለ የገለጸው ብልጽግና፥ አገር የሁላችንም ምሰሶ ናት፣አገር ከግለሰቦችና ከቡድኖች በላይ ናት፤እንደ አፈ ቀላጤዎቹ ቢሆንማ ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ልትኖር አትችልም ነበር ብሏል።
በሽብርተኛው ቡድን አማካይነት ለ27 ዓመታት ልዩነትን ብቻ እየጋተ ያሳደጋቸው ወጣቶች ሳይቀሩ ትርክቱን አሽቀንጥረው ጥለው፤ ለትህነግ አገራዊ ክህደት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሲሉ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድነት መዘምታቸውንም ጠቅሷል፡፡
ብልጽግና እንደገለጸው፥ አገር በምንም ልትተካ እንደማትችል የተረዱት እነዚህ ወጣቶች የአገራቸውን መለያ ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ላስተዋለ ሁሉ፥ የኢትዮጵያ ምንነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት በማያሻማ መልኩ ይገልጹለታል።
ጥጋብ አላስቀምጥ አላስተኛ ያለው ዘራፊናውና የሽብር ቡድኑ ትህነግ/ህወሃት ግን፥ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል ለመውረድ መዘጋጀቱን በአደባባይ እየዛተ እንደሚገኝ ጠቁሞ፥ ዳሩ ግን ኢትዮጵያን ያህል አገር ማፍረስ ከምኞት የዘለለ አይደለም ብሎታል ብልጽግና በጽሁፉ፡፡
ህወሃት በሚል የሽፋን ስም የሚንቀሳቀሰው ይህ ታጣቂ ሃይል የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ በማስቀደም አገርን ለከፋ አደጋ ለማጋለጥ ቆርጦ መነሳቱንም መግለጫው አሳውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!