የጡት ካንሰር ምልክቶችን በጊዜ ለመለየት የሚያስችል ቅድመ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል- ፕሬዚደንት ሣለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚደንት ሣለወርቅ ዘውዴ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወርን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት የጡት ካንሰር ምልክቶችን በጊዜ ለመለየት የሚያስችል ቅድመ ምርመራ ሁሉም እንዲደረግ አሳስበዋል።
የጡት ካንሰር ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠቃ ጠቁመው÷ በአገራችን ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱት ዘግይተው በመሆኑ ለዚሁ ግዛቤ ለመፍጠር እንዲረዳ የጥቅምት ወር የጡት ካንሰር ግንዛቤ ወር መባሉን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የሚታዩ ምልክቶችን በጊዜ ለመለየት ቅድመ ምርመራ እንዲደረግ የሚመለከታቸው ሁሉ በቂ ግንዛቤ ሊይዙ ይገባል ነው ያሉት ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ፡፡
ይህ ባለመሆኑ ብዙዎችን አጥተናል ብለዋል።
ከአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ለጨረርና ለኪሞ ሕክምና የሚመጡ ሴቶች መጠለያ ቦታ ስለሌላቸው ለተጨማሪ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም ለእነዚህ ሕሙማን ማረፍያ ቦታ በማዘገጀት፣ ወደ ሆስፒታል በማመላለስ፣ በመድሃኒት ግዢ በመደገፍ ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል “ፒንክ ሃውዝ” የተባለውን በቅርብ መጎብኘታቸውንም በመልዕክታቸው አንስተዋል፡፡
ይህንንና ተመሳሳይ ተቋሟትን በመደገፍ ሴቶች በጊዜ ከተደረሰበት ሊታከም በሚችል በሽታ እንዳይጎዱ እናድርግ ብለዋል፡፡
ህመሙን ቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም በጊዜ ወደ ህክምና ለመሄድ ራሳችን በዳሰሳ መመርመር፤ በጊዜ ወደ ሕክምና ጣቢያ እንሂድ፤ አቅም የሌላቸውን እንደግፋቸው የሚሉ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን ከፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት ያኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!