ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ልማት መረጋገጥ ኢትዮጵያ የበኩሏን ትወጣለች- አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ልማት መረጋገጥ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ህብረት አባል ሃገር የበኩሏን እንደምትወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት /ኔፓድ/ ያዘጋጀው መድረግ ተካሂዷል።
መድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ የኢትዮጵያን አቋም ማንፀባረቃቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፥ የአህጉሪቱን ዕድገት ዕውን ለማድረግ የህብረቱ አባል ሃገራት በ2063 ለተቀመጡት የዘላቂ ልማት ግቦች መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አጠቃላይ የአህጉሪቱን ለውጥ እና ዕድገት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ህብረቱ የፈጠረውን የትብብር ዕድል በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አስምረውበታል።