Fana: At a Speed of Life!

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች “የእሁድ ገበያ” መጀመሩን ከንቲባዋ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ “የእሁድ ገበያ” በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች መጀመሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
 
ገበያዎቹ በየሳምንቱ እሁድ የተለያዩ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ለከተማዋ ነዋሪዎች በአነስተኛ ዋጋ አንደሚቀርቡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
 
በዛሬው ዕለትም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ፣መገናኛ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ አደባባይና ቃሊቲ መናኸሪያ በርካታ ነዋሪዎች የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በመገበያየት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
 
በዚህም በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ቀጥተኛ እና አጭር የግብኝት ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ በዋናነትም ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪና ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር አስቀድሞ መከላከል ያስችላል ብለዋል።
 
በሁሉም የከተማችን አቅጣጫ የምትገኙ ነዋሪዎች በእረፍት ቀናችሁ በአቅራቢያችሁ ወዳሉት የእሁድ ገበያዎች በመሄድ መገበያየት እንደሚችሉም አመልክተዋል።
 
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ በተካሄደው የግብይት የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ እንደገለጹት÷የእሁድ ገበያው በከተማዋ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠርና በምርት አቅርቦትና ስርጭት የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መቀነስ ያስችላል።
 
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ስራ ማኅበራት፣ የሰብልና አትክልት አቅራቢዎች ፣የጅምላ ነጋዴዎች እና በምግብ ማቀነባበር የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራትና አምራች አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
 
በእሁድ ገበያው ከግብርና ምርቶች የጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች መቅረባቸው ተመላክቷል፡፡
 
በተጨማሪም ከኢንዱስትሪ ምርቶች ዘይት፣ ማካሮኒና ፓስታ እንዲሁም የባልትና ውጤቶች መቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.