የመከላከያ ሰራዊቱ ዛሬም ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 21፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሰራዊቱ ዛሬም ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛል ሲል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡
በደሴ ግንባር የተከሰተውን ሁኔታ በማስመልከት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ÷ መከላከያ የሚወስዳቸውን ስልታዊ እርምጃዎች በተሳሳተ መንገድ በመገንዘብም ሆነ ህዝብን ለማደናገጥ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ የህዝብ አንቂዎች እና ህዝብን የከዱ ባንዳዎችን መንግሥት ፈፅሞ አይታገስም ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሰሞኑን የኢትዮጵያ አየር ሀይል፣ የመከላከያ ሰራዊት ፣የአማራ ልዩ ሃይልና ህዝብ በወሰዱበት ተደጋጋሚ እርምጃ ከባድ መሳሪያዎቹ እና የቡድን መሳሪያዎቹ ወድመውበታል ፡፡
በመሆኑም የሽብር ቡድኑ ከሁሉም ግንባሮች ሀይሉን በማሰማራት የደረሰበትን ከፍተኛ ኪሳራ ለማካካስ እና መሳሪያዎችን ለመቀማት መጠነ ሰፊ የማጥቃት ሙከራዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሃል በትናንትናው እለት በደሴ ቡድኑ አስቀድሞ ያስገባቸው ሰርጎ ገቦች እና ሲቪል የቡድኑ ተልዕኮ አስፈጻሚዎች በመከላከያ ሀይሉ ላይ የኃላ ጥቃት ፈፅመዋል፡፡
ተግባሩ ብዙ እልቂት እንዳያስከትል የመከላከያ ሰራዊታችን ልዩ የማፈግፈግ ስልቶችን አድርጎ ዛሬም ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አሁንም ሰራዊታችን ከአማራ ልዩ ሀይል እና ከአማራ ህዝብ ጋር በመተባበር ይዞታውን ወደ ጭፍራ፣ወረባቦ እና በጋሸና በኩል በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ሚንስትሩ ዶክተር ለገሰ አስረድተዋል፡፡
ዛሬ በደሴ ግንባር እና በኮምቦልቻ ከፍተኛ ውግያ እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ክልሎች ያወጁትን የክተት ጥሪ በመቀበል ህዝቡ በቀረበለት ጥሪ መሰረት በመዝመት፣ የስንቅ ድጋፍ በማድረግ እና የተፈናቀሉትን በመደገፍ እንዲተባበር አሳስበዋል፡፡
ህዝቡ ውስጡ ያለውን ባንዳ በማውጣትም ደጀንነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡
በበርናባስ ተስፋዬ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!