Fana: At a Speed of Life!

ክልሉ በመኸር ወቅት የጀመረዉን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊዉ ድጋፍ ይደረጋል- አቶ ዑመር ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል በመኸር ወቅት የጀመረዉን ስራ በበጋ የመስኖ ስራም አጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ገለፁ፡፡

በሶማሌ ክልል በፋፈን ዞን አሮሬስ ወረዳ በኩታ ገጠም እርሻ የለማ የስንዴና የማሽላ ማሳዎች ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እና ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

በዘንድሮዉ የመኸር እርሻ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ ስንዴ መልማቱን፣ከዚህም 14 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ገልጸዋል፡፡

በፋፈን ዞን የተገኘዉን ልምድ ወደ አራት ዞኖች ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ኢብራሂም÷ በመኸር ከለማዉ ስንዴ ዉስጥ 50ሄክታር የዘር ብዜት መሆኑንና ሚኒስቴሩ ለክልሉ እየሰጠ ያለዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸዉ÷በሶማሌ ክልል ስንዴ በኩታ ገጠም እርሻ ለምቶ በማየታቸዉ መደሰታቸዉን እና ይህ አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር አካባቢዎች ላይ የኩታ ገጠም እርሻ በሁሉም ሰብሎች ማምረት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የክልሉን የመልማት አቅም በአግባቡ ከተጠቀምን አገራዊ የምርት ፍላጎትን ለማሟላት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ ጉልህ ድርሻ ሊኖረዉ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ክልሉ በመኸር ወቅት የጀመረዉን ስራ በበጋ የመስኖ ስራም አጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስቴሩ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ሁሉንም ስራዎች አመራሩ በባለቤትነት ከያዘ ዉጤታማ መሆን እንደሚቻል ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመዉሰድ የክልሉን የመልማት አቅም ለማሳደግ አመራሩ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ መቅረቡን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.