Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች ምርጥ ዘር እየተባዛ መሆኑን በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የማህበራዊ ምጣኔ ሀብትና የግብርና ኤክስቴንሽን ተማራማሪ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ ተናገሩ፡፡

የተለያዩ የስራ ሀላፊዎች የተሳተፉበት የሩዝ ምርት ምልከታ በምስራቅ ደንቢያ ተካሂዷል።

በምልከታው አቶ ሙሉጌታ÷ በአማራ ክልል ከ30 በላይ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች የቀረቡ ቢሆንም በሄክታር ምርታማነት ሻጋ የተባለው የሩዝ ዝርያ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል ነው ያሉት።

የሩዝ ምርት ሽፋኑም ሆነ መጠኑ እያደገ የመጣ መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪው የተለያዩ ምርታማነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ስራአስኪያጅ አቶ አስፋው አዛናው÷ ተቋሙ በሶስት ዞኖች በተለያዩ ዘርፎች የግብርና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሶስት ወረዳዎች በ210 ሄክታር ማሳ ላይ በሄክታር 50 ኩንታል ሩዝ ምርት የሚሰጠውን የሻጋ ዝርያ ዘር የማባዛትና ለአርሶአደሩ የማስተዋወቅ ስራ ማዕከሉ እየሰራ ነው ።

በምስራቅ ደንቢያ ሰራባ ዳብሎ ቀበሌ በ55 ሄክታር መሬት ላይ የተሻለ የሩዝ ዝርያ ዘር ብዜት የሰብል ቁመና መኖሩን በመስክ ምልከታ ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ዋና ስራአስኪያጁ በሺዎች የሚቀጠሩ አርሶአደሮቸን ዘር በመስጠት በምርት ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በቀጣይ ይከናወናል ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በዞኑ የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን ÷5ሺህ 200 ሄክታር መሬት በዞኑ በሩዝ ተሸፍኗል ነው ያሉት።

አርሶአደሮቹ በበኩላቸው÷ ከተሻሻለው የሩዝ ዝርያ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.