Fana: At a Speed of Life!

ከአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የተላለፈ የአስቸኳይ ጥሪ!

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትህነግ አሸባሪና ወራሪ ኃይል በአማራ ክልል ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየፈፀመ ህዝቡን እየገደለና እያዋረደ፤ ንብረቱን እየዘረፈ፣ እያወደመ እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ነው፡፡

ይህንን በተጨባጭ እየገጠመን ያለዉን የሕልዉና አደጋ ለመቀልበስ በመደበኛዉ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ብቻ ማሸነፍ የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ፤

የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደዉ 6ኛ ዙር፣ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትን የአስቸካይ ጥሪ ዉሳኔዎች አስተላልፏል፡፡

1. ከሚሰጡት አገልግሎት አስፈላጊነት አኳያ እየተመዘነ የሚወሰን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማንኛዉም የመንግስት ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን አቋርጦ በጀቱን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የገጠመንን የህልዉና ዘመቻ ለመቀልበስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲረባረብ ተወስኗል፣

2. ሁሉም የመንግስት ተሸከርካሪ ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለሕልዉናዉ ዘመቻ አገልግሎት እንዲዉል እንዲደረግ፣

3. የግል ተሸከርካሪ ባለቤቶች ለሕልዉና ዘመቻዉ ስኬት ሲባል በተፈለገ ጊዜ ሁሉ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ተወስኗል፣

4. በየደረጃዉ የሚገኝ አመራር የሕልዉና ዘመቻዉን ተቀብሎ የሚሰለፈዉን ሕዝብ አደራጅቶ ከፊት ሆኖ እየመራ ወደ ግንባር እንዲዘምት ይህን በማያደርጉ አመራሮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ተወስኗል፣

5. ሁሉም የመንግስትና የግል የጦር መሳሪያ የታጠቀ በሙሉ ለሕልዉና ዘመቻዉ አገልግሎት እንዲዉል ተወስኗል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛዉም የግል መሳሪያ የታጠቀ የክልሉ ነዋሪ በማንኛዉም ምክንያት በሕልዉና ዘመቻዉ ላይ የማይሳተፍ ከሆነ የታጠቀዉን የግል መሳሪያ በአደራ ለመንግስት እንዲያስረክብ ወይም እድሜዉ ለትግል ለደረሰ እና አካላዊ ጤንነት ላለዉ ለቤተሰብ አባሉ ወይም ለሌላ ሰዉ በማስተላለፍ ለህልዉና ዘመቻዉ አገልግሎት እንዲዉል እንዲያደርግ፣

6. በደጀንነት የሚገኘዉ ሕዝባችን ለሕልዉና ዘመቻዉ የሚያስፈልገዉን የሎጂስቲክስ አገልግሎት በማቅረብ የሕልዉና ዘመቻዉን ዉጤታማ እንዲያደርግ፣ በየደረጃዉ የሚገኘዉ አመራርም አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን አስፈላጊዉን እንዲፈጽም ተወስኗል፣

7. የሕልዉና ዘመቻዉን ተቀብሎ በግንባር ለመፋለም ከሚሰማሩት ዉጭ ያለዉ ማንኛዉም የክልሉ ነዋሪ በየአካባቢዉ ተደራጅቶ የአካባዉን ጸጥታ እንዲጠብቅ፣ ጸጉረ ለዉጦችንና ሰርጎ ገቦችን እንዲከታልና ለሕግ አስከባሪ አካላት አሳልፎ እንዲሰጥና ለሕልዉና ዘመቻዉ የበኩሉን ኃላፊነት ሁሉ እንዲወጣ፣

8. የህልዉናዉን ዘመቻ ዉጤታማ ለማድረግ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ላይ ለትግሉ በተለያየ መንገድ እንቅፋት በሚሆን ማንኛዉም ሰዉ ወይም ቡድን ላይ በየደረጃዉ እየተወሰነ የጸጥታ አካሉ አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወስድ ተወስኗል፣

9. የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸዉ ተቋማት ዉጭ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም፣

እነዚህን ዘጠኝ አስገዳጅ ዉሳኔዎች ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ በክልል ደረጃ በተቋቋመዉ የዘመቻ መምሪያ በሚቀመጥ አሰራር የሚወሰን ይሆናል፡፡

ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም

ባህር ዳር

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.