የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከካናዳ አቻቸው ፍራንስዋ ፍሊፕ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንስዋ ፍሊፕ ሻምፐኝ ጋር ተወያዩ።
በውይይቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያና ካናዳ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው፤ ካናዳ በኢትዮጵያ ልማት ዙሪያ ጠንካራ አስተዋፅኦ ካደረጉ ሀገሮች አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለችው ሁለንተናዊ ለውጥ ካናዳ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንዲትቀጥልም አቶ ገዱ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያና ካናዳ ከመንግስታት ትብብር ባሻገር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ትብብራቸውን ማስፋት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አክለውም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አምስት ቀን ወደ ካናዳ የሚያደርገው በረራ ለሀገራቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውሰው፤ ይበልጥ እንዲጠናከር ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የካናዳው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንስዋ ፍሊፕ በበኩላቸው፥ ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ፣ ረጅምና ታሪካዊ መሰረት ያለው መሆኑን አንስተው፣ በቀጣይም ተባብሮ ለመስራት ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደቸው ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ አድንቀው መጭው ምርጫም የተሳካ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀዋል።
ካናዳ ኢትዮጵያ ለያዘቸው የለውጥ ጉዞ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግም ካናዳ ዝግጁ መሆኗንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።