አልጄሪያ ለሞሮኮ የምትልከውን ጋዝ አቋረጠች
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አልጄሪያ ወደ ሞሮኮ የምትልከው ጋዝ ማቋረጧን አስታወቀች፡፡
ውሳኔው በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል፡፡
ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የወጣ መግለጫ “ሞሮኮ ሀገራችንን እና ብሔራዊ አንድነታችንን ንቃለች፤ በፈጸመችው የጥላቻ ድርጊትም ግንኙነታችንን ለመቀነስ እና ሶናትራች የተሰኘው የጋዝ ኩባንያ ከሞሮኮ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማቋረጥ ወስነናል” ይላል፡፡
የጋዝ መስመሩ የአልጄሪያን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞ በሞሮኮ በኩል በማለፍ ወደ ስፔን የሚያደርስ ነው፡፡
ሞሮኮም ጋዙን በማስተላለፍ ለምታበረክተው አስተዋጽኦ ክፍያ ስታገኝ ቆይታለች።
ከዚህ በተጨማሪም ሞሮኮ ከጋዙ የተወሰነውን በመጠቀም 10 በመቶ ያህል የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎቷን ለማሟላት ትጠቀምበት እንደነበረም ተመላክቷል፡፡
የአልጄሪያ ባለሥልጣናት በሞሮኮ ላይ ያዩትን ንቀት እና ጥላቻ ተከትሎ ከሀገሪቷ ጋር የነበራቸውን የጋዝ አቅርቦት የኮንትራት ውል እንዳይታደስ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ነው የተሰማው፡፡
አሁን አሁን የአልጄሪያ እና የሞሮኮ ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ሲሆን፥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውም ተቋርጦ ከሞሮኮ የሚደረጉ በረራዎች የአልጄሪያን የአየር ክልል እንዳይጠቀሙ እስከ ማገድ መደረሱን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
አልጄሪያ የራባት መንግስት በአልጄሪያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ይደግፋል፤ የእስራኤል ቴክኖሎጅን በመጠቀም በከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ስለላ ያደርጋል ስትል ትወነጅላለች።
በዓለማየሁ ገረመው