ደቡብ ጎንደር ዞን ሕዝባዊ ማዕበሉን በፍጥነት ማደራጀት መጀመሩን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ጎንደር ዞን ሕዝባዊ ማዕበሉን በፍጥነት ማደራጀት መጀመሩን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ÷ጠላት ወደ ዞኑ ለመግባት ካሰበበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ የነበረው ቁጣ እና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ጥሪ ካቀረበ በኋላ ትናንት ምሽት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ሁሉም ነገር ወደ ግንባር ሲል አውጇል።
የዞኑ አስተዳደር እና ሕዝቡ ጥሪውን ተቀብለው የመንግሥት ሠራተኛውን፣ ነጋዴውን ማኅበረሰብ፣ የታጠቀም ይሁን ያልታጠቀውን የኅብረተሰብ ክፍል አቅሙ እና እድሜው የሚፈቅድለትን በፍጥነት የማደራጀት ሥራ ተጀምሯል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።
እየተደራጀ ያለው ኀይል ቀጥታ ወደ ግንባር በመዝመትም በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ወገን ነጻ ለማውጣት ከሠራዊቱ ጋር ይቀላቀላል፤ ለዚህም በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ኅብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን የማወያየት እና ለቀጣይ ስምሪት የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የወጣቱ ስሜት ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት የተወረሩ አካባቢዎችን ነጻ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድንን እስከወዲያኛው ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆናቸውን አውስተዋል።
ከዚህ ባለፈም ግንባር ለተሰለፈው የፀጥታ ኀይል ተጨማሪ ጉልበት በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።
ዞኑ እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በወረራ ከፍተኛ ችግር ስለደረሰበት ሕዝቡ የጠላትን አስከፊነት ብቻም ሳይሆን የተወረሩ አካባቢዎችን እንዴት ነጻ ማድረግ እንደሚችልና የጠላትን አቅም ተረድቷል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
በከፍተኛ ወኔ፣ እልህ እና ተነሳሽነት ወደ ግንባር ለመሄድ የመጨረሻውን የድል ጽዋ ሊጎነጩ መነሳታቸውን ወጣቶች ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በበኩላቸው÷መስዋዕትነት ከፍለን ወራሪውን ትህነግ በመደምሰስ ነጻነታችንን እናረጋግጣለን ነው ያሉት።
ከአያቶቻችን የወረስነው ስለ ሀገር ፍቅር ራስን አሳልፎ መስጠት እና ስለ ሕዝብ ክብር መራራ መስዋእትነትን መጎንጨትን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!