ህብረተሰቡ በጊዜ የለኝም መንፈስ የክተት ጥሪውን በመቀበል ዘመቻውን መቀላቀል አለበት – የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁሉም አከባቢ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል በጊዜ የለኝም መንፈስ የክተት ጥሪውን በመቀበል የህልውና ዘመቻውን በፍጥነት እንዲቀላቀል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማውደም እና ለመበታተን ያቀደውን ዕቅድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማክሸፍ እየተሰራ ይገኛል፡፡
“ህብረተሰቡም ለክተት ጥሪው ምላሽ በመስጠት በየአካባቢያቸው በመመዝገብ ላይ ናቸው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይ የአማራ ክልል በትናንትናው ዕለት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በርካታ ታጣቂዎች ወደ ማዕከላት በመሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለክልሉ መንግስት ጥሪ አዎንታዊ ምለሾችን በመስጠት ወደ ግንባር ለማምራት በመደራጀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰቡ ምላሽ የሚያኮራ መሆኑን ጠቁመው፤ በጊዜ የለኝም መንፈስ ዘመቻውን በመቀላቀል መካላከያውን ማጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት አሁንም ህብረተሰቡን ደጀንነት በመጠባበቅ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በወሎ ግንባር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመው፤ የተፈጠረው የውጊያ መዛነፍ ሙሉ በሙሉ ተስተካክሎ ሰራዊቱ ለቀጣይ ተልዕኮ ራሱን ብቁ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ሰርጎ በገባባቸው ደሴ እና ኮምቦልቻ አከባቢዎች ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉን የገለጹት ዶክተር ለገሰ፤ በአሁኑ ወቅት የመንግስትንና የግለሰቦችን ንብረት በመዝረፍ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ትናንት ሌሊት ሰርጎ በገባበት ኮምቦልቻ ከተማ ከ100 ያላነሱ ወጣቶችን በረድፍ አሰልፎ መጨፍጨፉንም ጠቁመዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች የዘረፋቸውን ንብረቶች ጭኖ እንዳይወጣ ህብረተሰቡ መንገድ በመዝጋት መከላከል እና እንቅስቃሴውን መገደብ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱም አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የህብረተሰቡን አንድነት ለመሸርሸር እና የመከላከያ ሰራዊቱን እንቅስቃሴ ለማወክ ሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በእነኚህ አካላት ላይ እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ መጀመሩን ገልጸው፤ ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በኦሮሞ ልዩ ዞን በቦርከና ዳዋ ጨፌ አካባቢዎች በትናንትነው ዕለት “ሕወሀት እየመጣ ነው” በሚል የአሸባሪው የሸኔ ሀይል መንገድ የመዝጋት እና ሌሎች አፍራሽ ድርጊቶችን ለመፈፀም ቢሞክርም በአካባቢው ወጣቶችና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ዓላማውን ማክሸፋቸውን ገልጸዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!