Fana: At a Speed of Life!

የከዳተኞችን ቅስም ሰብረን ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር ሁላችንም በያለንበት ወታደር ልንሆን ይገባል – የፌዴሬሽን ም/ቤት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ጥቅምት 24 የክህደት ጥግ የታየባት ዕለት! የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ልብ የሰበረ ዜና የተሰማበት ዕለት ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ዛሬም የከዳተኞችን ቅስም ሰብረን ሀገራችን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር ሁላችንም በያለንበት የሀገራችን ወታደር ልንሆን ይገባል – የፌዴሬሽን ምክር ቤት

ጥቅምት 24 የክህደት ጥግ የታየባት ዕለት! የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ልብ የሰበረ ዜና የተሰማበት ዕለት ነው፡፡

ታሪክ ታሪክ ሠሪዎቿን ትመስላለች፡፡

ዕቡያንና እኩያን በእብለታቸውና በክህደታቸው ይታወሳሉ፡፡

ለእውነት የቆሙና አገርን ያስቀደሙ ደግሞ በእውነትነታቸውና በርትዕትነታቸው ይዘከራሉ፡፡

ሁለቱም ግን የታሪክ አካል ናቸው፡፡

ሁለቱም የዓለምን የታሪክ ስንክሳር ስንገልጥ የምናገኛቸው ናቸው፡፡

‹ከባቄላ አይጠፋም ዲቃላ፣ ከጠላ አይታጣም አተላ› እንደሚባለው በኢትዮጵያ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥም ዕቡያንና እኩያን በቅለው ሀገራቸውን ወግተዋል፤ ወገናቸውንም ጎደተዋል፡፡

ሆኖም የቆሙበት ዓላማ እውነትና ርትዕት ስላልነበረ በቡቃያነታቸው ሊጠፉ ግድ ሆኗል፡፡

የታሪክ ድርሳኖች ግን እኩይ ግብራቸውን ይዘክራሉ፡፡

ከዘመናችን የክህደት ጥጎች መካከል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የተፈጸመውን የሚስተካከል ፈጽሞ የሚገኝ አይመስልም፡፡

ይህችን ዕለት ለሀገር ዳር ደንበር ለመስዋዕትነት የቆመው ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በራሱ ወገኖች ከጀርባው የተወጋበት በመሆኗ በታሪክ ጠባሳነት ሁሌም ስንዘክራት እንኖራለን፡፡

አበው እንዲህ መሰሉ ድርጊት ሲገጥማቸው ‹ሁለተኛ ግፌ ጫንቃ ተገርፌ፣ ልብሴን መገፈፌ› ይላሉ፡፡ በመከላከያችን ላይ የሆነውም ይኼው ነበር፡፡

በግፍ ላይ ግፍ፣ በበደል በደል፣ ከሁሉም በላይ የሚያመው ደግሞ ግፉ የተፈጸመው ህልውናችሁን ለመጠበቅ ስል ሕይወቴን ለመስዋዕት ከሃያ ዓመት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ በቆየላቸው ወገኖች መሆኑ ሲታሰብ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያመው ድርጊቱ ለዘመናት ታፍራና ተከብራ የኖረችን አገርና የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያዋረደ መሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይህችን ዕለት ሲያስታውሱ ለሕልውና ዘመቻው የራሳቸውን ድርሻ እንዴት ሊወጡ እንደሚችሉ በማሰብ ሊሆን ይገባል፡፡

በታሪክ የኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች፤ ሁሉንም ግን እንደአመጣጡ ተቀብላ በድል ተወጥተዋለች፡፡

ህልውናዋንም አስጠብቃ ዘመናትን ተሻግራለች፡፡

ዛሬም የከዳተኞችን ቅስም ሰብረን አገራችን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር ሁላችንም በተሰማራንበት የሙያ መስክ የሀገራችን ወታደር ልንሆን ይገባል፡፡

የከዳተኞች ጀንበር ጠልቃ እውነት ደምቃና ፈክታ የድል ጮራ አስክትወጣ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን አሸባሪንና ወራሪውን የጁንታ ቡድን ልንዋጋው ይገባል፡፡

የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝቦች!

“ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት”!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.