የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ወራሪውን ለመፋለም ተዘጋጅተዋል – የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብርተኛውን ትህነግ ወራሪ ቡድን ለመደምሰስ ከአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የተላለፈውን የክተት ጥሪ ተከትሎ የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በግንባር ለመፋለም ዝግጅት መጀመራቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ አስታወቁ፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ተደርገው ማንኛውም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ የዞኑ ማኅበረሰብ ግንባር ለመሰለፍ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪው ያስታወቁት፡፡
ወጣቶች ግንባር ከመዝመት ባለፈ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሰርጎ በመግባት የሽብር ሥራ ለመሥራት የሚሞክሩ አካላት ላይም እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሀገሪቱን ለማፍረስ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ ታደሰ ይህንን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ የመላው ኢትዮጵያውያንን የጋራ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ በጋራ በመሰለፍ ሁሉም ሀገሩን ሊታደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዞኑ አሸባሪውን ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ዘመቻ ሁሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አሚኮ ዘግቧል፡፡