Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳዉን አሸባሪ ቡድን ደምስሰን ሃገራችንን እናድናለን – የጭልጋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በግንባር ተሰልፌ በመፋለም የራሴን አስተዋጽኦ አደረጋለሁ እንጅ ቤቴ ድረስ እስኪመጣ በመጠበቅ የታሪክ ተወቃሽ መሆን አልፈልግም ትላለች በምዕራብ ጎንደር ዞን የአይከል ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ና ርዶስ አለሙ።
ወጣቷ መንግስት ያደረገውን የክተት ጥሪ ተቀብላ ለመዝመት ዝግጁ መሆኗን ጠቅሳ፤ ይህንን የሃገርና የህዝብ ጠላት የሆነ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል በግንባር በመሰለፍ ለመፋለም መዘጋጀቷን ነው ለኢዜአ የጋለጸችው።
በዘመናዊ መሳሪያና ወታደር በውጭ ጠላት የተፈጸመውን ጥቃት ባልተደራጀ የሰው ኃይል ማሸነፍ የተቻለው በህዝባዊ አንድነት እንደሆነ የምትናገረዉ ወጣቷ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጠላትን ለማስወገድ የሚያደርጉት የህልውና ትግል በድል እንደሚጠናቀቅም ያላትን እምነት ትገልጻለች።
በዞኑ ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብላታ ጥላሁን በበኩላቸው፤ አሁን ያለው ትውልድ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ሀገሩን ከጥፋትና ከመፍረስ መታደግ ይኖርበታል ይላሉ።
ኢትዮጵያ ለመላዉ ጥቁር ህዝብ መመኪያ ለአፍሪካ ኩራት የሆነችው አባቶቻችን በአንድነት በመቆም በዘመናዊ የጦር መሳሪያና አደረጃጀት የተዋቀረውን ሀያል ሀገር ጣሊያንን በማሸነፋቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ብላታ ከውጭ ጠላት ጋር በማበር የሀገሪቱን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት የሚጥሩ ሀይሎችን በአንድነት ለመከላከል በሚደረገውን ዘመቻ ላይም እንደ አንድ የዚህ ዘመን ትዉልድ የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡
ሌላው የነባሪ ጭልጋ ወረዳ ነዋሪና የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት አቶ ደሴ መኮንን እንደተናገሩት ያላቸውን ልምድ በመጠቀም ወደ ግንባር ለመሄድና ዛሬም እንደትናንቱ በደማቸው ታሪክ ለመፃፍ ወስነዋል።
ሀገሬን እወዳለሁ ማለት በቃላት ብቻ ሚገለጽ አይደለም ያሉት ነዋሪው አቅሙና ችሎታው ያለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወደ ግንባር በመሄድ ሀገሩን ማዳን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሀገርን ከወራሪ መታደግና ሉዓላዊነቷን ማስጠበቅ የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ለሃገራቸው ክብርና ዝና ሲሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
የህውሃት የሽብር ቡድን ከዚህ በላይ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ መፍቀድ አይገባም ያሉት ደግሞ በዞኑ መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ እያዩ ተዋበ ናቸው።
ለሀገር መሞት ክብር ነው ያሉት አቶ እያዩ የክልሉ መንግስት ያቀረበውን የክተት አዋጅ በመቀበል ወደ ወሎም ይሁን ሌላ ግንባር ለመሄድ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ዘመቻው የህልውና በመሆኑ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚችለውን በማድረግ ማሸነፍ ግዴታ የሆነውን ትግል በጋራ በመትመም ሀገርን ማዳን ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.