Fana: At a Speed of Life!

አንድ ሆኖ በመቆምና አቅምን በማስተባበር የሽብር ቡድኑን ህልፈት ማፋጠን ይገባል-የሐረሪ ክልል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
አሸባሪው ህውሓት ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የመከላከያ ሃይላችን ላይ ታሪክ የማይረሳው ክህደት ከፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ሁሉንም አይነት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
 
አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያግዙትን የውጭ ጠላቶችና ከእናት ጡት ነካሽ የውስጥ ተላላኪዎችን አስተባብሮ በሁሉም አቅጣጫ ውጊያ ከፍቶብናል።
 
በጦርነቱ ጎረቤት የሆኑ ክልሎችን በሁሉም አቅጣጫ በመውረር በርካታ ጥፋቶችን አስከትሏል፡፡ አሁን ላይ በሁሉም ግንባር ጦርነት በማካሄዱ በርካታ የሰው ሀይሉ ተደምስሶበታል ያለ የሌለ ሀይሉን በሙሉ ወደ ወሎ ግንባር ከህጻናት እስከ አዛውንት ወንድና ሴቶች ፤ አካልጉዳተኞች ና ነፍሰ ጡሮች ፤ የሀይማኖት አባቶች ሳይቀር እያስገደዶ አዝምቷል፡፡
 
ወራሪውና አሸባሪው ቡድን ወደር የሌለው ጭካኔ በመላበስ በየደረሰበት አካባቢ ሴቶችን በመድፈር ፤ ንጹሀንን በመረሸን ፤ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ፤ የግልና የመንግስት ሀብቶችን በመዝረፍ እንዲሁም እንስሳትን በጥይት እየገደለ ጠላትነቱን በይፋ አሳይቷል፡፡
 
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን በመቆም ሃገራችንን መታደግ የግድ ከሚለን የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነን እንደ ሃገርም ቁርጠኛና የተናበበ አመራር ከምንሰጥበትና የተደራጀ የህዝብ ንቅናቄ ከምናረጋግጥበት የትግል ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን።
 
በህዝባዊ ማእበል የመጣን ሀይል ጀግናው የመከላከያ ሀይላችን እና ህዝቡ በጋራ እየተናበቡ በመመከት ድልም እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ሆኖም ቡድኑ ተስፋ የቆረጠ እና አጥፍቶ መጥፋት ስልት እየተከተለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ጥፋት ሳያደርስ ግበአተ-መሬቱን በመፈጸም የሰላም አየር መተንፈስ ይገባናል፡፡
 
ለዚህ ደግሞ በክልላችን የተጀመረውን ድጋፍና አለኝታነት አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን ህዝቡም የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል ፤መዝመት የሚችል ወጣት ወደ ግንባር ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡና ስንቅ በማዘጋጀት እንዲሁም አካባቢን በንቃት በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
 
የሀረሪ ክልል የህወሃት ዘራፊ ጁንታ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ቀጥተኛ ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ አመራሩን ፣ ባለሃብቱንና መላ የክልሉን ነዋሪዎች በማስተባበር ለመከላከያ ሃይላችን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
የክልሉ መንግስት ዛሬም በየግንባሩ በጽናትና በጀግንነት የሚፋለሙት የመከላከያ ሰራዊታችንና መላ የጸጥታ ሃይሎቻችን ጠንካራ ደጀን ከመሆን ባሻገር አመራሩንና ህዝቡን በማስተባበር በግንባር በመሰለፍ ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት አብሮአቸው ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
 
በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ ከህዝቡና ከሁሉም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በግዜ የለኝም መንፈስ እንደሚሰራም በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል።ህወሀት አቅሙ ቢኖረውና ቢችል መላው ኢትዮጵያን መውረርና መበታተን ፍላጎቱ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን አምርረን በመታገል የማይቀረውን ድል ማፋጠን ይገባናል።
 
ሀገርን በጦርነት ተሳትፎ ከማዳን ጎንለጎን እየተከናወኑ ያሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክረን በመስራት እንዲሁም አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ለጸጥታ አካላት በመጠቆም የአካባቢያችንን ሰላም መጠበቅ ይገባናል።
በመጨረሻም ለዚህ ወሳኝ ትግል መላው የክልላችን ነዋሪዎችና መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ ወሳኝ ወቅት አንድ ሆነው በመቆምና ሁለገብ አቅማችሁን በማስተባበር የሽብር ቡድኑን ህልፈት ለማፋጠን የሚያስችል ፈጣንና ወሳኝ እርምጃ እንድትወስዱ ጥሪውን ያስተላልፋል።
 
ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትቀጥላለች!
 
የሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
 
ጥቅምት 22/2014
 
ሐረር
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
 
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.