የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ

By Melaku Gedif

November 02, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የመዲናዋ የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሽብርተኛው የህወሃት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፥ ሀሰተኛ መረጃ የሚያስተላለፉ እና የሚያስተጋቡ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥብቅ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የሽብር ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በሰሜን ዕዝ ላይ ከፈፀመው ጥቃት ባለፈ ሀገር የማፍረስ ዓላማውን አጠናክሮ በመቀጠል ሀገሪቷን የእልቂት አውድማ ለማድረግ መረቡን ዘርግቶ ቢንቀሳቀስም በህዝብና በፀጥታ አካላት ትብብር ዓላማው እየከሸፈ ነው  ብሏል ግብረኃይሉ በመግለጫው ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ አስመልክቶ የደህንነትና ጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ አውጥቷል፡፡