Fana: At a Speed of Life!

በህዝቦች መራራ ትግል የተገኘው ለውጥ በባንዳዎች አይደናቀፍም- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከለተው ቀርቧል።
 
በኢትዮጵያ ህዝቦች መራራ ትግል የተገኘው ለውጥ በውስጥ ባንዳዎች አይደናቀፍም!

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሻባሪው የህወሓት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በጎጥ ከፋፍሎ ሲመዘብር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቡድን እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ አትኖርም በሚል እሳቤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለ የሌለውን ኃይል አሰባስቦ ዘምቶብናል።

ባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት በህዝቦች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘውን ሀገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ ጊዜያት ሞክሮ ያልተሳካለት ይህ አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚገኘውን የሰሜን እዝ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኢትዮጵያውያን በይፋ መውጋት ከጀመረ ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላው ዋዜማው ላይ እንገኛለን።

በሰሜን ዕዝ ጥቃት እጅግ የተቆጣው የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና መላው ህዝባዊ የፀጥታ ሃይሎቻችን በወሰዱት የሕግ ማስከበር ዘመቻ የጥቃቱ ጠንሳሾችና ባለቤቶችን ለሕግ ማቅረብ፣ እርምጃ በመውሰድና የቀሩትን መበተን ቢቻልም፣ በሕግ ማስከበሩ የተጎዱ የትግራይ አከባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና አርሶ አደሮች እርሻቸውን ተረጋግተው እንዲያርሱ የተወሰደውን የአንድ ወገን ተኩስ አቁም አሸባሪ ቡድኑ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በመላው የአፋር እና የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ወረራውን አስፋፍቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ጁንታው የትህነግ ቡድን በፈጸማቸው አረመኔያዊ ጥቃቶች ንጹሐን ተገድለዋል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ በሰው ልጅ ላይ ለመፈፀም ቀርቶ ለማሰብ የሚከብዱ አስነዋሪ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈፀም እኩይ ተግባሩን በግልጽ ከማሳየቱም አልፎ ለዘመናት የተገነቡ የህዝብ መሰረተ ልማቶችን በመዝረፍና የቀረውን በማውደም ኢትዮጵያን ለማዋረድና ሀገራችንን ለማፍረስ እኩይ ተግባሩን በስፋት ቀጥሎበታል። በሴት እህቶቻችን ላይ አሳዛኝና አስነዋሪ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተፈጽሟል።

ይህ ቡድን ከተቻለ ኢትዮጵያውያንን በኃይል በማንበርከክ ወደ ቀድሞ ስልጣን ለመመለስ ካልሆነ እሱ ያልመራትን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ የማይፈልጉ ታሪካዊ የውጪ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎችን አስተባብሮ የክህደት ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በዜጎች አልህ አስጨራሽ መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ በአልባሌ መንገድ አሸባሪው ህወሓት ጁንታ ቡድን መና ለማስቀረት የሚያደርገው ጥረት በአይበገረው ህዝባችናን ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡

ስለሆነም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ድርድር የማያውቀውን የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ሳይለያይ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የያዘውን እቅድ በአማራና አፋር ክልል ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥፋት በጋራ ይመክታል።

በተላላኪዎቹ አማካይነት በውክልና ጦርነት በክልላችን ቡድኑ የሚያደርገው መፍጨርጨር በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በፀጥታ ኃይላችንና በህዝባችን የተባበረ ክንድ እየተመከተ በመሆኑ ውርደትን እየተከናነበ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የክልላችን ብልጽግና ፓርቲ አመራሩ፣ አባሉና መላው የክልላችን ነዋሪዎችን በማስተባበር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሰው ኃይል፣ በአይነት፣ በገንዘብና በሞራል እየደገፈ የቆየ ቢሆንም ካለው ወቅታዊ አሳሳቢ የህልውና ጉዳይ ይህንን የህዝባችን ጠላት የሆነውን የጥፋት ቡድን ግብዓተ- መሬቱን ለማፋጠን የጀመርነውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

በክልሉ ለሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፡-

ጁንታው የህወሓት ቡድን ከስም ያለፈ ለትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ የተለየ የጠቀመው አንድ ነገር በሌለበት፣ የትግራይ ክልል ህዝብ ኢትዮጵያዊ ወንድም ህዝብ ነው ብለን ባለንበት፣ ነገር ግን በደሴና በኮምቦልቻ ከጉያችን ውስጥ ሆነው አስተኳሽና ከሃዲ ባንዳዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል፡፡ ስለሆነም በክልላችን ብሎም በሀገራችን የምትገኙ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ከዚህ እኩይ ተግባር ራሳችሁን አቅባችሁ ከኢትዮጵያ ወገን ህዝቦች ጋር እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ለመላው የክልላችን ህዝቦች፡-

የልማታችን ፀር የሆነውን የጁንታውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ደምስሰን ፊታችንን ወደ የልማት ተግባሮቻችን ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ መላው የክልላችን ህዝቦች ከሀገር መከላከያ ጎን እንዲቆሙ የክልሉ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል።

ለክልሉ ወጣቶች፡-

ሀገር የምትቀጥለው በትውልዶች ቅብብሎሽ ነው፡፡ ጁንታው የህወሓት ቡድን ሀገርን ለመምራት የሚጥረው በእውቀትና በአስተሳሰብ ልዕልና በትውልዶች ቅብብሎሽ ሳይሆን ባረጀና ባፈጀ እሳቤ አንድ ትውልድ ለዘላለም በስልጣን ላይ ማስቀጠል መሆኑን ወጣቶቹ ተገንዝበን ሀገርን ለማዳን በሚደረግ ትግል ውስጥ የወጣቱ ትግል የጎላ ሚና ስላለው የመከላከያ ሰራዊት እና የክልሉን ፀጥታ ኃይል በመቀላቀል ሀገራዊ ተልዕኮን እንዲወጡ እየጠየቅን፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሠላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በንቃት እንዲጠብቁና የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ ሥራ እንዲያጠናክሩ ለማሳሰብ እንወዳለን።

ለክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፡-

የህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ምህዳር ጠቦ ከምርጫ በኋላ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እስራት ይጠብቅ የነበረው ታሪክ ተቀይሮ በብልጽግና ፓርቲ ዘመን ከለውጥ በኋላ ማለትም ከ6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በፊትና በኋላ የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደጠላት ከመፈረጅ ይልቅ በአመራር መዋቅር ውስጥ አካትቶና ስልጣን ሰጥቶ በትብብርና በቅንጅት በመስራት ረገደ ብልጽግና ፓርቲ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጀብድ ሰርቷል፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ምህዳሩንና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን እንዲያብብ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶችን ለማስወገድ በሚደረግ ትግል ውስጥ የበኩላችሁን እንድትወጡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

ለፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች፡-

በሀገር ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት በሚደረግ ጥረት ውስጥ በክልላችን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰና ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባችሁ ፓርቲያችን ያስገነዝባል። የጋራ ሰላም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት አመራሩ አገራዊ ግዴታው እንዲወጣ ፓርቲው ያሳስባል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት

 

አሶሳ

 

አካባቢዎን ይጠብቁ!
 
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
 
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
 
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
 
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
 
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
 
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
 
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
 
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.