የሀገር ውስጥ ዜና

ሁሉም ህብረተሠብ ጁንታዉን ለመቅበር የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

By Meseret Awoke

November 02, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የጁንታዉ የጦርነት አላማ ኢትዮጵያን ማፍረስና ህዝቡን ለባርነት መዳረግ ስለሆነ ሁሉም ህብረተሠብ ጁንታዉን ለመቅበር የሚጠበቅበትን እንዲወጣ የጋምቤላ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ።

የጋምቤላ ክልል እና የጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ÷ አሁን የምንገኝበት ነባራዊ ሀቅ ህዝቦችን በማንነታቸው ለይቶ ለማጥፋት አቅዶ ከተነሳ እና ሀገርን ለመበታተን ቆርጦ ከተነሳ አሸባሪ ቡድን ጋር እየተፋለምን የምንገኝበት ወቅት ነው ብለዋል።

ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥፋት አስቦና አቅዶ የተነሳን ሀይል ማሸነፍ የሚቻለው እንደ ህዝብ አንድ ሆኖ በመቆምና በመመከት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል።

አሁን የገጠመንን ችግር ለመሻገርም ሆነ የነገንም በማሰብ የፀጥታ ሀይላችንን ማጠናከር በሁሉም አካባቢ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ተቀዳሚ ተግባር መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጠላት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ይህንንም ህዝብ እንዲረዳው ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ላክዴር ላክባክ በበኩላቸው ÷ የአሸባሪው ሕወሓትና የሸኔ አላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን መገንዘብ እና መታገል ያስፈልጋል ብለዋል።

ጠላት የመጨረሻ እድሉን አሟጦ እየተጠቀመ ያለበት ሰዓት በመሆኑ በሀሰት ከሚራገቡ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች ራሳችንን በመጠበቅ ሁሉም በህልውናው ላይ የመጣን አደጋ ለመቀልበስ ራሱን ማዘጋጀት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

አንዳንድ አመራሮች በሰጡት አስተያየት ÷ እንደሀገር የገጠሙ ችግሮችን ለማለፍ በአንድነትና በሙሉ አቅም መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የአሸባሪውን ተላላኪዎች በተደራጀ መንገድ በማጋለጥ የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ እንዲሁም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመራሮቹ ማመልከታቸውን ከክልሉ መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!