Fana: At a Speed of Life!

በሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5 /2014
በሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
መንግሥት የሃገርን ህልውና፣ ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤
የሽብርተኛው ሕውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹ እንቅስቃሴ በሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ ጉልህ እና ድርስ አደጋ የደቀነ በመሆኑ፤
ሽብርተኛው ሕውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹ ለዕኩይ አላማቸው መሳካት በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀሙ ያሉት ግድያ፣ ዝርፍያ እና ሌሎችም ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢሰብዐዊ ጥቃቶች እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ከግምት በማስገባት፤
ከቀጥተኛ እና መደበኛ የውግያ አውድ በተጨማሪም የሽብርተኛው ሕውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹን ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች ከሰላማዊ ዜጎች ጋር በመመሳሰል በህዝብ እና በሃገር ላይ የደቀኑትን ከፍተኛ እና ተጨባጭ የደህንነት ስጋት በመረዳት፤
ሽብርተኛው ሕውሃት ኢትዮጵያን የማዳከም እና ብሎም የማፍረስ ምኞት ካላቸው የውጭ ሃይሎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እየሰራ እንደሆ በመገንዘብ ፤ ከላይ የተገለፁት የሃገር ህልውና ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ እና ተግባራዊ ማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል::
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
1. አጭር ርእስ
ይህ አዋጅ “የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል::
2. ትርጓሜ
ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል፣
1. “የሕግ አስከባሪ አካል” ማለት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ
የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልል ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ማለት ነው።
2. “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ” ማለት የዚህን አዋጅ አፈጻጸም ለመከታተል እና በበላይነት ለመመራት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7 መሠረት የተቋቋመ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ ነው።
3. “የጦር መሳሪያ” ማለት በጦር መሳሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር
1177/2012 ትርጉም የተሰጣቸውን አነስተኛ፣ ቀላል እና ሌሎችንም
የጦር መሳሪያ አይነቶች እና ጉዳት አድራሽ ዕቃዎች ያጠቃልላል።
4. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው
አካል ማለት ነው።
5. በዚህ አዋጅ በወንድ አነጋገር የተገለፀው ሴትንም ይጨምራል።
3 የተፈፃሚነት ወሰን
1.ይህ አዋጅ በመላው ኢትዮጵያ ተፈፃሚ ይሆናል።
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የአደጋው መጠን እና አካባቢያዊ አድማስ እየቀነሰ በሄደ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን በዚያው ልክ እየጠበበ ሊሄድ የሚችል ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ አዋጁ ተፈፃሚነት በከፊልም ሆነ በሙሉ ቀሪ የሚሆንባቸውን አካባቢዎች በመመሪያ ይወስናል፣ ይህንኑ ለሕዝብ ያሳውቃል።
ክፍል ሁለት
በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የማይፈቀዱ ተግባራት
4. በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት፣ እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ደህነንት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፦
1. በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ
የጸጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ
ይችላል፤
2. እድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱ እና የጦር መሳርያ
የታጠቁ ዜጎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ
እንዲቀበሉ፣ ወይም ይህን ማድረግ የማይችሉ ሲሆን በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግስት እንዲያስረክቡ ሊያዝ ይችላል፤
3. የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን ይችላል፤
4. ማናቸውም የህዝብ የመገናኛ እና የህዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ
ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል፤
5. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ
የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ
አዋጅ ተፈፃሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይችላል፤
6. ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ
የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን
ማናውንም ቤት፣ ህንፃ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣
ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፤ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሳሪያዎችን መውረስ ይችላል ፤
7. ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት
እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ
እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቀቁ ለማዘዝ ይችላል፣
8. ከፍተኛ የፀጥት ችግር እና ስጋት በተፈጠረባቸው የሃገሪቱ ክፍሎች
የአካባቢ አመራር መዋቅርን በከፊልም ሆነ በሙሉ፣ ማገድ፣ መለወጥ እና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት ይችላል፤
9. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራልም ሆነ የቁስ ድጋፍ
ያደርጋል ብሎ የሚጠረጥረውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት
እንቅስቃሴ በሚመለከተው ባለስልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም
ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፤
10.በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራል ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚያምነውን የመገናኛ ብዙሃንን ወይም ጋዜጠኛ በሚመለከተው ባለስልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፤
ተመጣጣኝ ሀይል ስለመጠቀም እና የማይታገዱ መብቶች
1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በዚህ አዋጅ የተመለከቱ
የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን ለማስፈጸም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሕግ
አስከባሪ አካላት ተመጣጣኝ ኃይል እንዲጠቀሙ መመሪያ ለመስጠት ይችላል።
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎችም፣
በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግስቱ አንቀፅ
93(4)(ሐ) መሰረት ሊታገዱ የማይችሉ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎችን እና
መብቶችን ማክበር ይኖርበታል።
የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎች
1. ሁሉም ሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በአዋጁ መሰረት
የሚያወጣቸውን መመሪያዎች እና የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች የመቀበል ግዴታ አለበት።
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጁን አላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት
አስተዋፅዖ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጭት የተከለከለ ነው።
3. በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች
የገንዝብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።
4. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው
አካላት ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።
5. ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወይም ሌሎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው የፀጥታ አካላት ወይም ከነዚህ አካላት እውቅና እና ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
6. በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ የመንጃ ፈቃድ፣ የሰራተኛ
መታወቂያ፣ ፓስርፖርት ወይም ከነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙመንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
ከነዚህ የመታወቂያ ሰነዶች መካከል የትኛውም የሌለው ሰው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ ዝርዝር የአፈፃጸም መመሪያ ባወጣ በሁለት ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የቀበሌ፣ የወረዳ የፀጥታ እና አስተዳደር ፅህፈት ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ በመመዝገብ ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታ አለበት።
7. ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ
የስራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከለከለ ነው።
8. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ የተከለከለ ነው።
ክፍል ሶስት
ስለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መቋቋምና ኃላፊነት
1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ
ኢታማገዥር ሹም የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሟል።
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመርያ ዕዙ መዋቅር እና አደረጃጀት በጠቅላይ
ሚኒስትሩ የሚወሰን ይሆናል።
3. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ እና
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነት ወስደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈፃሚ
የሚያደርጉ ግብረሃይሎችን ወይም ኮሚቴዎችን ሊያቋቁም ይችላል።
4. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ ተጠሪነት ለ ኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ።
5. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 የተመለከቱ
እርምጃዎችን ተፈጻሚነት ይመራል፣ ይከታተላል።
6. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በሃገሪቱ የሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላትን በአንድ ዕዝ ሥር አድርጎ በላይነት ያስተባብራል፣ ይመራል፣ ያዛል።
7. ኃላፊነቱን ለመወጣት ሌሎች አስፈላጊ እና አግባብ የሆኑ ስልጣኖች ይኖሩታል።
ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
8. ተፈፃሚነታቸው የታገዱ ሕጎች
1. በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እሲኪጠናቀቅ
ድረስ የትኛውም የዳኝነት አካል ስልጣን አይኖረውም።
2. በቪዬና ኮንቬንሽን የተመለከተው የዲፕሎማቲክ መብት እንደተጠበቀ
ሆኖ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጎች ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተፈፃሚነታቸው ታግዶ ይቆያል::
9. የወንጀል ተጠያቂነት
1. የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን
ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደጥፋቱ ክብደት እስከ አስር አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።
2. የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን
በመተላለፍ የተፈፀመው ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣት
የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።
3. በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙ የአዋጁ እና በአውጁ ማዕቀፍ
የወጡ መመሪያዎች ጥሰቶች የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ ቢያበቃም፣ የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት በመደበኛው የወንጀል ሥነ ስርዐት ሕግ መሰረት ይቀጥላል።
10. መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በአዋጁ የተሰጠውን ስልጣን
ተግባራዊ ለማድረግ እና ሃላፊነቱን ለመወጣት አስፈላጊ መመሪያዎችን
ያወጣል።
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የሚወጡ መመሪያዎች ተፈፃሚ
ከመደረጋቸው በፊት ለህዝብ በስፋት ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ
እንዲተዋወቁ መደረግ ይኖርበታል።
11. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
1. ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ
ጀምሮ ለስድስት ወራት የፀና ይሆናል።
2. የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር
ቤት የአዋጁ ተፈፀሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል።
አዲስ አበባ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ/ም
ዐብይ ኣሕመድ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር
May be an image of 1 person
30,807
People reached
3,434
Engagements

-1.8x Lower

Distribution Score
Boost Post
1.4K
57 Comments
253 Shares
Like

 

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.