Fana: At a Speed of Life!

‘ታሪካችን የአሸናፊነት ነው’!- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባወጡት መግለጫ ‘ታሪካችን የአሸናፊነት ነው’! ሲሉ ገልጸዋል።
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
‘ታሪካችን የአሸናፊነት ነው’!
ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የመንግስትነት ታሪክ ያላት፤ የጥንታዊ እና ገናና ስልጣኔዎች ባለቤትና እና መገኛ፤ የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ እና የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ናት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዚያት ከቅርብ እና ከሩቅ ጠላቶች እየተነሱባት ሉዓላዊነቷን ለመድፈር፤ ነጻነቷን ለመግፈፍ ጥረት ቢያደርጉም ጠላቶቿን በጀግንነት በመመከት እና የህዝቦቿን አንድነት እና ነጻነቷን አስከብራ በትውልድ ቅብብሎሽ ታፍራና ተከብራ ለዓለም ሁሉ የነጻነትና የጽናት ተምሳሌት የሆነች ናት፡፡
የውጭ ጠላቶቿ ሀገራችንን ሲፈታተኑ የእናት ጡት ነካሽ በመሆን አባሪ ተባባሪ ሆነው ሀገራችንን የሚወጉና የሚያስወጉ የውስጥ ባንዳዎችም ነበሩ፡፡ ይሁንና አርበኛ ልጆቿ በተባበረ ክንድ ጠላቶቿን እያሳፈሩ የወራሪዎችን እና የባንዳዎችን ቅስም በመስበር አኩሪ ተጋድሎ በመፈጸም እስከዛሬ ደርሰናል፡፡
በታሪክ እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ጦርነቶችን ብታካሂድም አንድም ጊዜ የሌሎችን ሉኣላዊነት በመዳፈር ወይም ጠብ አጫሪ በመሆን ስሟ ተነስቶ አያውቅም፡፡ በአንጻሩ ድንበር ጥሶ ክብራችንን እና ሉዓላዊነታችንን ለመዳፈር የመጣብንን ጠላት እና ተባባሪ ባንዳ ተገቢውን ቅጣት ቀጥተን ድል መንሳትን እናውቅበታለን፡፡
ለዚህም ታሪካችን ምስክር ነው፡፡
ለእኛ ለኢትዪጵያውያውን የድላችን እና የአሸናፊነታችን ዋና ምስጢር አንድነታችን ነው፡፤ በውስጥ ጉዳያችን ባልተስማማንባቸው ጊዚያት ሁሉ ሳይቀር ሀገርን ለማፍረስ የመጣን ወራሪ ወይም የውስጥ ባንዳ ልዩነታችንን በይደር አስቀምጠን አንድ ሆነን ጠላትን ድል መንሳት ታሪካችን ብቻ ሳይሆን መታወቂያ ማንነታችን ጭምር ነው፡
ህወሃት መራሹ መንግስት ለሃያሰባት አመታት ልዩነታችንን በማጉላት እና ሀገራዊ አንድነታችን በማኮሰስ የአይበገሬነት ምንጫችን የሆነውን አንድነታችንን ለማፍረስ ያልወጣው ዳገት፤ ያልወረደው ቁልቁለት አልነበረም፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ በበላይነት የተቆጣጠረውን የመንግስት መዋቅር በመጠቀም የዘረፋ እና የአፈና ተግባራትን ሲያከናውን የኖረ ዘራፊ እና አፋኝ ቡድን ነው፡፡
መላው የሀገራችን ህዝብ ይህ ጸረ ዴሞክርትና ዘራፊ ቡድን አንገሽግሾት ከዳር አስከዳር ሆ ብሎ በመነሳት ባካሄደው ህዝባዊ ትግል አስከወዲያኛው እንዳይመለሰ አድርጎ ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ ጥሎታል፡፡
ባለፉት ሶስት የለውጥ አመታትም የለውጡ ሃይል ለሀገራችን አንድነት እና ብልጽግና ተረጋግቶ እንዳይሰራ በተለያዩ መንገዶች ጸረ አንድነት፣ ጸረ ሰላም እና ጸረ ልማት እኩይ ሰይጣናዊ ተግባራቱን ሲያካሂድ ቆይቷል ፤እያካሄደም ነው፡፡
ይባስ ብሎ የሀገራችን ኢትዮጵያ ጋሻና መከታ የሆነውን እና በትግራይ ክልል ከሃያ አመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ሀገሩን እና ህዝቡን ከጥቃት ሲጠብቅ የኖረውን፤በክልሉ የልማት ስራዎች በገንዘቡ፤ በጉልበቱ እና በህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደረግ የቆየውን እና ከትግራይ ወገኑ ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረውን ጀግናውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባልተጠበቀ ጊዜ አድብቶና አዘናግቶ በማጥቃት እጅግ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ጦርነትም አውጆብናል፡፡
በዚህ ድርጊቱም ይህ አሸባሪ የጥፋት ኃይል ጸረ ኢትዮጵያነቱን በተግባር አስመስክሯል፡፡ ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስትና መላው ህዝብ ህግ የማስከበር ዘመቻ በማካሄድ በአጭር ጊዚ እና በአንስተኛ ኪሳራ አሸባሪውን ሃይል በመደምሰስ ለጥፋት ሀይሉ ባንዳዊ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ሰጥተዋል፡፡
መንግሰት ለመላው የትግራይ ህዝብ ባለው አክብሮት እና መልካም ሀሳብ የተነሳ የተናጥል የተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ክልል የወጣ ቢሆንም አሸባሪው ህወሃት ግን ቆሜለታለው ለሚለው ህዝብ እንኳን ደንታ ቢስ እንደሆነ በአስመሰከረ መልኩ ጦርነቱን በመቀጠል ወደ አጎራብች ክልሎች ዘልቆ በመግባት ከሰብዓዊ ፍጡር ፈጽሞ የማይጠበቁ አረመኔያዊ እና ሰይጣናዊ ድርጊቶችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ይህ ቡድን በማናቸውም ጊዚያት እና ታሪክ ተደርጎ የማያውቅና ሊናገሩት እንኳን የሚያሳፍር ተግባራትን አከናውንል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን ጨፍጭፏል፡፡ ቤተ እምነቶችን አቃጥሏል፡፡ የሀይማኖት አባቶችን አዋርዶ ገድሏል፡፡ ሴቶችን በእናቶቻቸው፤አባቶቻቸው፣በልጆቻቸው እና በባሎቻቸው ፊት ደፍሯል፡፡ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፡፡ እንስሳትን ዘርፎ ከመብላት ባሻገር በጥይት ረሽኗል፡፡ መንገድ በመዝጋት እና ድልድይ በመስበርም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችም እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡ይህ ቡድን የሀገራችንን ገጽታ በማበላሸት ሀገር የማፍረስ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ይህ የጥፋት እኩይ ቡድን ከነዚህም በላይ በሰው አእምሮ ለማሰብ የሚከብዱ ዘግናኝ ድርጊቶችን በሰላማዊ ኢትዮጵያዊያን ላይ ፈጽሟል፡፡ እየፈጸመም ነው፡፡
እኔ በበላይነት አዛዥ ናዛዥ የማልሆንባት ኢትዮጵያ ትፍረስ፡፡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን በማለት ሀገራችንን ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሰራ ያለው አሸባሪ ምርጫ እንዳይካሄድና ሀገራችን መንግስት አልባ እንድትሆን የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶችን በማስተባበር እየዘመተብን ይገኛል፡፡
ይሁንና ለሉኣላዊነቱ ፍጹም ቀናኢ የሆነው ህዝባችን ምርጫውን ማሳካት ችሎ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ተኣማኒነት ያለው ምርጫ በማካሄድ የራሱን መንግስት መስርቷል፡፡
አሸባሪው ጁንታ ለሰላም የተዘረጋን እጅ ባለመቀበል ጠባብ ፍላጎቱን በጉልበት እና በጦርነት ለማስፈጸም የሄደበትን ርቀት ስንመለከት የህዝባችን እና የመንግስታችንን አርቆ አስተዋይነትና ሆደ ሰፊነትን የሚፈታተን ነው፡፡
ስለሆነም ህዝቡ እንደራሴ ብሎ የመረጠን እኛ የህዝብ ተወካዮች በወቅታዊው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በጥልቀትና በስፋት ከተወያየን በኋላ የሚከተለውን ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
1. የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም. በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት ፈጽሞ ትግራይ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እሰካደረሰበት እለት ድረስ የኢፌዴሪ መንግስት ላሳየው ታጋሽነት፤ ለሰላም ያደረገውን ጥረትና አርቆ አስተዋይነት ከፍ ያለ እውቅና እና አክብሮት እንሰጣለን፡፡ አሸባሪው ቡድን የመንግስትን ለሰላም እና ለአንድነት ተብለው የተደረጉ ጥረቶችን ወደ ጎን በመተው ሀገርን የማፍረስ ተልዕኮ አንግቦ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት ከፈጸመ በኋላ የኢፌዴሪ መንግስት ለወሰደው አፋጣኝ ምላሽ እና የህግ ማስከበር ዘመቻም አድናቆት አለን፡፡ስለሆነም ከአሸባሪው ህወሃት ጋር የሚደረገው ጦርነት ማስቀረት ፈልግን ልናስቀረው ያቻልነው ተገደን የገባንበት ሀገርን ከመፍረስ የመታደግ ፍትሀዊ ተጋድሎ በመሆኑ እኛ የኢፌዴሪ የህ/ተ/ም/ቤት አባላት ከመከላከያ እና ከመላው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባባር ከህዝባችን በጋር በመሆን አስፈላጊውን ተቋማዊ እና የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን፡፡
2. ኢትዮጵያን እየመራ ያለው መንግስት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ እና ነጻ ምርጫ የተመረጠ የመላው ኢትዮጵያውያን ይሁንታን ያገኘ ህዝባዊ መንግስት ነው፡፡ ስለሆነም አሸባሪው ህወሃት እና ተላላኪው ሸኔ ያልተቀደሰ ጋብቻ እና ሀገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ በጽኑ እያወገዝን የምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ኃላፊነታችንን ከወትሮው በላቀ ዝግጁነትና ትጋት በመወጣት ሀገርን ከእነዚህ አሸባሪ ኃይሎች ከመታደግ ባሻገር ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ እውን በማድረግ ታሪካዊ እና ህገ መንግስታዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡
3. እኛ ኢትዮጵያውያን የአንዳቸን ህመም ለሁላችን ህመም እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ የምንድነውም በጋራ ነው፡፡
በህግ ማስከበረና ሀገርን በማዳን ተግባር ተሰማርተው ለተጎዱና ውድ ህይወታቸውን ጭምር ለሀገራቸው መስዋዕትነት ለከፈሉ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት እና ለመላው የሀገራችን ጸጥታ ኃይሎች አባላት ከፍ ያለ ክብርና እውቅና እንሰጣለን፡፡ አሸባሪው ኃይል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከህዝባችን እምነት፣ ባህል፣ ስነ ልቦና እና ታሪክ ባፈነገጠ መልኩ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ እያወገዝን በጥፋ ኃይሉ ወላጆቻቸውን ለተነጠቁ፤ አካላቸው ለጎደለ፤ አንጡራ ሀብታቸውን ላጡ፤ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻቸን ወደ ነበሩበት ተመልሰው ሙሉ በሙሉ እስኪቋቋሙ ድረስ አምኖ እና ፈቅዶ ከወከለን ህዝባችን ጋር በመሆን እና ያልተቋረጠና ተከታታይነት ያለው ድጋፍና እርዳታ ለማስተባበር እና የድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
4. የሰላም አማራጮችን ሁሉ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጥርቅም አድርጎ ስለዘጋ በተባበረ ክንድ ጠላቶቻችንን ከመቅበር ውጨ አማራጭ የለንም፡፡ ስለሆነም በተወከልንባቸው አካባቢዎች በመሰማራት እና በመዝመት መላውን ህዝባችንን ለጸረ – ህወሃት ትግል በማንቀሳቀስ እና በማስተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችንን ከአሻባሪው ሐይል የማጽዳቱ ስራ እንዲሳካ የበኩላችንን ድርሻ
5. ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሸባሪው እና የውጭ ግብረአበሮቹ የተከፈተባትን ሀገርን የማፍረስ ጦርነት በመረዳት ከጎናችን ለቆሙ ወዳጅ ሀገራት ከፍ ያለ አክብሮታችንን እንገልጻለን፡፡ እንዲሁም በጁንታው እና በአፈ ቀላጤዎቹ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ምክንያት የተሳሳተ አረዳድና አቋም ለያዙ ሀገራትም ትክክለኛውን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት ፍትሃዊ አቋም እንዲይዙ የሚያስችል እና የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ለማስቻል የፓርላመንተሪ ዲፕ.ሎማሲ ስራዎቻችንን አጠናክረን እንሰራለን፡፡ የጁንታው የጡት አባት በመሆን ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ ሀይሎችን ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለሉአላዊነታችን እና ለነጻነታችን ያለንን ቀናኢነት እንዲረዱ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችለን የዲፕሎማሲ መንገድ እንዲከተሉ እንመክራለን፡፡
6. አሸባሪው ሃይል ስግብግብ ፍላጎቱን ለማሟላት በትግራይ ወገናችን ስም ለሃያ ሰባት አመታት በስሙ ሲነግድ እንደቆየ እኛ የኢፌዴሪ የህ/ተ/ምቤት አባላት እንረዳለን፡፤ አሁንም ይሄው አሸባሪ ቡድን የራሱን ጠባብ ፍላጎቶች በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ለመጫን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ማስፈጸሚያ መሳሪያ በማድረግ የትግራይን እናት እያስለቀሰ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የትግራይ ወንድም ህዝብ ከጁንታው ራሱን በመነጠል እና ከመላው ወንድምና እህት የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን መንግስት እያደረገ ያለውን ሀገርን የማዳን ስራ ውስጥ ተሳታፊ ይሆን ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
7. መረጃን ከትክክለኛ ምንጮች ብቻ በመውሰድ እና ለጠላት የሀሰት ወሬ ቦታ ባለመስጠት፤ የመንግስት መዋቅር በሚሰጠን አቅጣጫ መሰረት ማናቸውንም አስፈላጊ ግብአቶች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሀይላችን በማቅረብ፤ አካባቢያችንን በንቃት በመየጠበቅ እና በተሰማራንበት ሁሉ ተግተን በመስራት የጠላትን ሴራና የተጋረጠብንን አደጋ ለማክሸፍ ከመንግስት ጎን እንደትሰለፉ ለመላው የሀገራችን ህዝብ ለኢትዮጵያ ወዳጆችና የልማት አጋሮች ጥሪያችንን እናስተላልፋልን፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 23/2014
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ! ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
May be an image of text that says 'የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት HOUSE OF PEOPLES'REPRESENTATIVES OF THE FDRE'
0
People reached
204
Engagements
Distribution Score
Boost Post
177
3 Comments
24 Shares
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.