በቻይና በአንድ ቀን ብቻ 97 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ለህልፈት ተዳረጉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና በትናንትናው ዕለት ብቻ 97 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ።
ይህ ቁጥር እስካሁን በቀን ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛው ሲሆን፥ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር 908 አድርሶታል ተብሏል።
በአጠቃላይ በቻይና በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 40 ሺህ 171 የደረሰ ሲሆን 187 ሺህ 518 ግለሰቦች ደግሞ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 3 ሺህ 281 ሰዎች ህክምና ተደርጎላቸው አገግመው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ ያለበትን ሁኔታ የበለጠ ለመመርመር የህክምና ባለሙያዎችን እና ተመራማሪዎችን የያዘ ቡድን ወደ ቻይና መላኩም ነው የተገለፀው።
በቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ እና ስራ ዝግ እንዲደረግ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት በርካቶች ወደ ስራ ገበታቸው እንደተመለሱ ታውቋል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision