የሀገር ውስጥ ዜና

በእንጦጦ ፓርክ ተጨማሪ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ እየተገነባ ነው

By Alemayehu Geremew

November 03, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን 390 መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማስቆም የሚያስችል 14 ሺህ 449 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመኪና ማቆሚያ በእንጦጦ ፓርክ አካባቢ እየገነባ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

የመኪና ማቆሚያው በሦሥት የተለያዩ ቦታዎች በልዩ ትኩረት እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የተመላከተው፡፡

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የመጀመሪያው ክፍል በእንጦጦ ፓርክ ዋና በር ፊት ለፊት የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘው ሁለተኛው የመኪና ማቆሚያ ሥፍራም በተመሳሳይ በእንጦጦ ፓርክ መግቢያ በር አጠገብ የሚገኝ ሲሆን በ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ የሚገኝ እና 60 መኪናዎችን ማቆም የሚያስችል ነው፡፡

አሁን ላይም የግንባታው የአፈር ቆረጣ ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

የመጨረሻው ግንባታ ደግሞ 6 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ስፋት የሚሸፍን ሲሆን በአንድ ጊዜ 220 መኪኖች ማቆም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በሱሉልታ መስመር ላይ እየተገነባ የሚገኘው ይህ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ በእንጦጦ ፍተሻ በኩል የሚመጡ ትን የእንጠጦ ፓርክ ጎብኚዎች ታሳቢ ያደረገ ግንባታ እንደሆነም ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡