Fana: At a Speed of Life!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መዋቅር እና አደረጃጀት መመሪያ ይፋ ሆነ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትመን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ ማጽደቁን ተከትሎ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መዋቅር እና አደረጃጀት መመሪያ ይፋ ሆኗል፡፡

 

በዚሁ መሠረት “የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014” ተብሎ ነው ይፋ የሆነው፡፡

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መዋቅር እና አደረጃጀት መመሪያውም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መዋቅር እና አደረጃጀት መመሪያ

የአስቸኳይ ጊዜ 5 /2014 መመሪያ ቁጥር 1/2014

“የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 5/2014”፣ አንቀጽ 7 (1) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም፣ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ተጠሪ የሆነ በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ያቋቋመ ሲሆን ÷ በዚሁ
አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ(2) አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምርያ ዕዙ መዋቅር እና አደረጃጀት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን እንደሆነ ተመላክቷል።

በዚሁ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ መዋቅር እና አደረጃጀት እንደሚከተለው እንዲሆን ተወስኖ ይህ መመሪያ ወጥቶዋል።

1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ መዋቅር እና አደረጃጀት
እነዚህ መሰረት በፌደራል እና በክልል ደረጃ የአዋጁን አፈፃፀም እንዲከታተሉ ከዚህ በታች የተመላከቱት ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፤

1) የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክትትል ኮሚቴ፤
2) የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የፀጥታ ኮሚቴ፤
3) የክልል’ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ፤
2) ተጠሪነት

ከዚህ በላይ የተመለከቱት ኮሚቴዎች ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። ኮሚቴዎቹ የስራ አፈፃጸማቸውን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ሪፖርት ያቀርባሉ።

3. የኮሜቴዎቹ ሃላፊነት

4. በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የአዋጁን አፈፃፀም እንዲከታተሉ የተቁቋሙት ኮሜቴዎች ሃላፊነት እንደሚከተለው ይሆናል፤

ሀ) የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክትትል ኮሚቴ ሃላፊነት፤

1.የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ጋር በተገናኘ ያሉ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ማስተባበር እና መከታተል፤

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ ለማሳካት የሚሰሩ የህዝብ አደረጃጀት እና እንቅስቃሴ ስራዎችን ማስተባበር እና መከታተል፤

3. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ጋር በተገናኘ የሚኖሩ የህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ፤

4. በሽብርተኛው ቡድን የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ማሳለጥ፤

ለ) የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የፀጥታ ኮሚቴ ሃላፊነት፤

1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የቀን ተቀን አፈፃፀም በፌዴራል ደረጃ መምራት፣ ማስተባበር እና መከታተል፤

2. በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ ክልከላዎች እና ግዴታዎችን ተፈጻሚነት ማረጋገጥ፤

3. ሁሉንም ፀጥታ፣ የደህንነት እና የህግ አስከባሪ አካላት በተቀናጀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል፤

4. ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሳካት አስፈላጊ የሆኑ ኦፕሬሽኖችን በቅንጅት ማቀድ እና ተግባራዊ ማድረግ፤

ሐ) የክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ ሃላፊነት

1. በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅሙ ግብረ-ሃይሎችን ማቋቋም፤

2. በክልል ደረጃ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ጋር በተገናኘ ያሉ የፖለቲካ እና የህዝብ ግንኙነንት ስራዎችን ማስተባበር እና መከታተል፤

3. በክልል ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ ለማሳካት የሚሰሩ የህዝብ አደረጃጀት እና እንቅስቃሴ ስራዎችን ማስተባበር እና መከታተል፤

4. በክልል ደረጃ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ጋር በተገናኘ የሚኖሩ የህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ፤

5. በክልል ደረጃ በሽብርተኛው ቡድን የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ማሳለጥ፤

6. ከፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የፀጥታ ኮሚቴ ጋር በተናበበብ መንገድ በክልሉ የፀጥታ ማስክበር ስራዎችን መምራት፣ ማስተባበር እና መከታተል፤

4) የኮሜቴዎች ስብጥር

በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የአዋጁን አፈፃፀም እንዲከታተሉ የተቁቋሙት ኮሜቴዎች ስብጥር እንደሚከተለው ይሆናል፤

ሀ) የፌዴራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክትትል ኮሚቴ

1. አቶ ደመቀ መኮንን (ም/ጠ/ ሚኒስትር እና የው/ጉ/ሚኒስትር) – ሰብሳቢ
2. ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ – አባል
3. አቶ በለጠ ሞላ – አባል
4. አቶ አቶ ቀጀላ መርዳሳ – አባል
5. ኢንጂነር አይሻ መሐመድ – አባል
6. ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ – አባል
7. ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ – አባል
8. አቶ ሬድዋን ሁሴን – አባል
9. አቶ ምትኩ ካሳ – አባል

ለ) የፌደራል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የፀጥታ ኮሚቴ

1. ጄ/ል ብርሃኑ ጁላ( የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም) – ሰብሳቢ
2. የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል – አባል
3. የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር – አባል
4. የፍትህ ሚኒስትር – አባል
5. የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት – አባል

ሐ) የክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ

1. የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር – ሰብሳቢ
2. የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር – ም/ሰብሳቢ
3. የክልሉ የፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ – አባል
4. የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር – አባል
5. የክልሉ ፍትህ ቢሮ/ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ – አባል

አዲስ አበባ 24/2/2014
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.