የኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሩ ምርት በቀጥታ ለሸማቹ እንዲደርስ እየሠራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአርሶ አደሩን የግብርና ምርት በቀጥታ ለአዲስ አበባ ሸማቾች ለማቅረብ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡
የተፈጠረው ምህዳር ÷ ለኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ከመፈጠሩም በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እንዲቀርብላቸው ያስችላል ሲሉ የገለጹት በምክትል ርዕሰ- መስተዳድር ማዕረግ የመንግስት ኃብት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ናቸው፡፡
በዕሁድ ገበያው የክልሉ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለመዲናዋ ነዋሪዎች እንዲያቀርቡ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ከፍተኛ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑም ዶክተር ግርማ ተናግረዋል፡፡
የአርሶ አደሮቹ ምርቶችም በተመረጡ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች መገበያያ ቦታዎች፣ ሳር ቤት በሚገኘው የኦሮሚያ ቢሮዎች ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲሁም በፑሽኪን አደባባይ ለግብይት ይቀርባሉ ነው የተባለው፡፡
አሁን ላይ እንደ ቲማቲም፣ አቮካዶ እና ፓፓያ ያሉ ትኩስ ምርቶች ከአምራች ገበሬዎች ለመዲናዋ ሸማቾች እየቀረቡ እና እየተገበያዩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ምርቶቹም በፍጥነት የሚበላሹ ስለሆነ መንግስት ሳይበላሹ ለተጠቃሚው እንዲደርሱ የሚያስችሉ ማቀዝቀዣዎችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በቀጣይም ምርቶቹን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ግርማ የተናገሩት፡፡
የመዲናዋ ነዋሪዎች በተመቻቸላቸው የዕሁድ ገበያ በቀጥታ የአምራች ገበሬዎችን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበዩ እንዲሁም የሚቀርቡትን ትኩስ ምርቶች እንዲጠቀሙ መልዕክት ተላልፏል፡፡
በያደሳ ጌታቸው
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!