የሀገር ውስጥ ዜና

”ጨቅላ ልጄን ትቼ የምዘምተው ልጄን ለማሳደግ አገር ስለሚያስፈልግ ነው”

By Meseret Awoke

November 04, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ 60 ሠራተኞቹን ዛሬ ወደ ግንባር ሸኝቷል።

ሰራተኞቹ በተለያዩ የጦር የአገልግሎት መስኮች ያገለገሉ ናቸው ዛሬ ወደ ግንባር ይተሽኙት።

ሽኝት ከተደረገላቸው የድርጅቱ ሠራተኞች መካከል የቀድሞ ሠራዊት አባል ሃምሳ አለቃ ዳባ ደረጄ አንዱ ናቸው።

ሃምሳ አለቃ ዳባ ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶችና በውስጥ ባንዳዎች የተከፈተባት ጦርነት እንደ ዜጋ ቁጭት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

“አይቼ ያልጠገብኳት የስድስት ወር ጨቅላ ህጻን ብትኖረኝም ትቻት ለመዝመት የወሰንኩት ልጄን ለመመገብና ለማሳደግ ቅድሚያ አገር ስለሚያስፈለግ ነው” ሲሉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የአሸባሪው ህወሓት አቅም እንደሚያወራው ሳይሆን በሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን በማታለልና ውዥንብር በመፍጠር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ዘማቾቹ የአስር አለቃ አበበ ግርማ እና ግርማ ወርቁ ናቸው።

የሽበር ቡድኑ ከንቱ ህልምና አገር የመበተን ዓላማ በቅርቡ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ግብዓተ መሬቱ ይፈጸማል ሲሉም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ጠላት ከሚነዛው የሀሰት መረጃ በመራቅ፣ መከላከያ ሠራዊቱንና የጸጥታ ሃይሉን ከመደገፍ ባሻገር ድሉን ቅርብ በማድረግ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ መስራት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።

ነገር ግን አሸናፊነት የሚመጣው በመንግስት ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም በየአካባቢው የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎችን በመከታተል ማጋለጥ ይገባል ብለዋል ዘማቾቹ።

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ገበየሁ ወርቁ ብዙዎች ኢትዮጵያን የመበታተንና ኃይሏን የማዳካም ዓላማ ይዘው ቢነሱም በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ መኖሯን አውስተዋል።

አሁንም የውስጥና የውጭ ጠላቶች አገሪቷን ለማዳከም የሚያደርጉትን ጥረት በጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ብርቱ ትግል እንደሚመከት ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ስትወጋ ማየት ህመም ሆኖባቸው የዘመቱ ሠራተኞች ደመወዛቸውና ሌሎችም ጥቅማጥቅሞች እንደሚከበሩላቸውና ድርጅቱ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚንከባከብ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዘማቾቹ ከድርጅቱ የወሰዱት የገንዘብ ብድር ካለ እንዲሰረዝላቸው መወሰኑንም ገልጸዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!