በደቡብ ክልል መሳሪያ የታጠቀ ግለሰብ በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲያስመዘግብ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ማንኛውንም የጦር መሳሪያ የታጠቀ አካል ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አምስት ቀናት ማስመዝገብ እንደሚገባው ተገለጸ።
የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ፥ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ትናንት ያካሔዱትን ውይይት መድረክ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በሀገራችን የተቃጣውን ወረራ ለመመከት የክልሉ መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለውን ጉዳት በመደበኛው ህግ ማስከበር ባለመቻሉ በመላው ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ሃላፊዋ፥ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር ውጤታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የአመራሩ ሚና ምን መሆን እንዳለበት በስፋት መወያየት መቻሉን ጠቁመዋል።
አመራሩ እራሱን የህልውና ዘመቻው አካል በማድረግ መላውን ህዝብ በማስተባበር የተቃጣብንን ወረራ መመከት እንደሚገባም ከስምምነት ላይ መደረሱን ወይዘሮ ሰናይት በመግለጫቸው አስረድተዋል።
ህዝባዊ ማዕበል በመፍጠር ህብረተሰቡ የመከላከያው እና የልዩ ሀይሉ ደጀን እንዲሆን መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የህልውና ዘመቻውን አመራሩ በብቃት መምራት እንዲችል ዝርዝር ውይይት የተካሔደ ሲሆን ፥ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ፣ የሰርጎ ገቦችን እንቅስቃሴ መከታተል እንዲችል ማደራጀት እና መምራት ይገባልም ሲሉ በመግለጫቸው አብራርተዋል።
እንደ ሀላፊዋ ገለጻ አመራሩ በትኩረት ከተወያየባቸው ነጥቦች ውስጥ የክልሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም አተገባበር በብቃት መምራት ሲሆን ለዚህም የክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዝ በስፋት የተወያየ ሲሆን ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት ማንኛውም የጦር መሳሪያ የታጠቀ አካል ከዛሬ ከጥቅምት 26 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ቀናት በአካባቢው በሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች ቀርቦ ማስመዝገብ ይኖርበታል ብለዋል።
እንዲሁም ማንኛውም መታወቂያ የሚሰጥ አካል አዲስ መታወቂያ መስጠት አልያም የመታወቂያ እድሳት ማካሔድ ክልክል መሆኑን ጠቁመዋል።
አስቸጋሪ ሁኔታ ቢፈጠር እና መታወቂያ ማግኘት ግዴታ ሆኖ ከተገኘ ግን የክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ እዝ አውቆት ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችልም አብራርተዋል።
ወይዘሮ ሰናይት አክለውም በሀገራችን የተቃጣውን ወረራ እጅ ለእጅ ተያይዘን መመከት ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አለመሆኑን አስረድተዋል።
መላው የክልሉ ህዝቦችም ይህንን ወራሪ ሀይል ግብአተ መሬት ለማፋጠን የጀመሩትን የህልውና ዘመቻ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

0
People reached
0
Engagements
–
Distribution Score
Boost Post
Like
Comment
Share