Fana: At a Speed of Life!

13ኛው ሀገር አቀፍ የከተሞች የውሃ ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012(ኤፍ.ቢ .ሲ) 13ኛው ሀገር አቀፍ የከተሞች የውሃ ፎረም በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለፀ።

ፎረሙ “የራስን አቅም በማጠናከር በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድም ታውቋል።

የፊታችን የካቲት 9 እና 10 2012 ዓ.ም ለሚካሄደው ፎረም ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።

ፎረሙ የውሃ አገልግሎት ተቋማት እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ በማድረግ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር ለህብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት እንዲያበረክቱ የሚረዳ ነው ተብሏል።

የሶዶ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ፋንታ እንደገለጹት፥ በከተማዋ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ፎረም አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል።

የፎረሙ ዋነኛ ዓላማ ከተሞች ተሞክሮ እንዲለዋወጡ ማስቻልና በንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የወላይታ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ባለፈው በጀት ዓመት ለደንበኞቹ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን በማቅረብ ከሀገሪቱ ከተሞች ከደሴ ቀጥሎ ሁለተኛው መሆኑ ይታወቃል።

13ኛው ዙር ሃገር አቀፍ የከተሞች ውሃ ፎረም ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ወደ 1 ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎች እንደሚገኙም ይጠበቃል።

በአስጨናቂ ጉዱ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.