Fana: At a Speed of Life!

ፖሊስ ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለሽብር ተግባራት ሊውሉ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ፖሊስ ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለተለያዩ የሽብር ተግባራት ሊውሉ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች መያዙን ገለፀ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ 208 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መጀመሩንም ፖሊስ ገልጿል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት እና ለውጥ ስራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ በሰጡት መግለጫ÷ በድሬዳዋ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች ላይ በሁለት ቀን በተካሄደ ኦፕሬሽን ከህወሓት እና ከሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው 208 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አብራርተዋል፡፡
በግለሰቦቹ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በተደረገ ብርበራ አምስት ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር፣ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ የኢትዮጵያ ብር፣ የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ፣ ፈንጂ ማቀጣጠያ ገመዶች፣ የተለያዩ የሚሊተሪ አልባሳት እና ትጥቆች፣ ሞባይል፣ ላፕቶፖች፣ ፓስፖርት፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ መቅረጸ-ድምጽ፣ ሀሺሽ፣ ማህተም እና የተለያዩ ሰነዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማን ጸጥታ ለማረጋገጥ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት እና ከድሬዳዋ ህብረተሰብ ጋር የተቀናጀ ስራ በመስራቱ አመርቂ ውጤት መገኘቱን የገለጹት ኮማንደሩ÷ ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ማሳሰባቸው ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የውስጥም ሆነ የውጭ ጸረ-ሰላም ሃይሎች በሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጦርነት ለማምከን የድሬዳዋ ህብረተሰብ አካባቢውን በሚገባ በመጠበቅ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት አለበት ያሉት ኮማንደር ገመቹ÷ የህወሃት እና የሸኔ ሃገር የማፍረስ ምኞትን ለመቅበር በሚደረገው ሁሉ አቀፍ እንቅስቃሴ ሁሉም የድሬዳዋ ነዋሪ መሳተፍ አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የከተማውን ጸጥታ ለማረጋገጥ እየሰራ ሲሆን÷ ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፖሊስ አባል ወይም በፖሊስ የመረጃ ስልክ ቁጥሮች ላይ በመደወል የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ኃላፊው ጨምረው አሳስበዋል፡፡
የከተማውን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር ተከታታይነት ያለው የውይይት መድረክ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ጥሩ ግብአት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.