አሸባሪውን ኃይል በተባበረ ክንድ መቅበር ይገባል- በአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አሸባሪውን ኃይል በተባበረ ክንድ መቅበር ይገባል- በአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን የአቋም መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሀገራት ሰላምና ሕልውና ዘብ የቆመችባቸው ወቅቶች ከታሪክ ድርሳናት ሲመዘዝ የትዬሌሌ፣ ምን አልባትም ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋት ነው፡፡ ኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሦማሊያ እና ሌሎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለአፍሪካውያን፣ ለመላው ጥቁር እና ጭቁን ሕዝብ ከባርነትና ጭቆና መላቀቅ ሚናዋ በታሪክ ፊት ከፍ ብሎ የሚጠቀስ፣ ለውጭ ወራሪ ኃይሎች ያልተደፈረች፣ በታሪካዊው የዐድዋ ድል ዓለምን ያስደመመች፣ ለወዳጆቿ ጠብ እርግፍ የምታውቅ፣ በጸብ ለሚመጡባት ደግሞ የሚደቁስ ክንዷን የምታሳርፍ ብርቱ ሀገር ናት፡፡
ይህ ሁሉ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር አሁን የውስጥ ሰለሟ ተናግቶ ሕዝቧ በመፈናቀል፣ በጅምላ ፍጅት፣ በረሃብና ጦርነት የሚታወቅና እርዳታ ሰጪ ሳይሆን ተቀባይ፣ የሌሎች ሰላምና ጭቆና አስጨንቋቸው የሚዘምቱ ሳይሆን “ሰላም አደሩ ወይ?” ተብሎ የሚታዘንላቸው ሆነናል፡፡
የዚህ ሁሉ ሳንካና ምስቅልቅል ዐቢይ መነሾው ደግሞ የጎሳና የጉልበት ፖለቲካ ነው፡፡ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት አብዶ ፍላጎቱን ሁሉ በኃይል ለመጫን የሚሞክር ስብስብ እምር ብሎ ተነስቶ የቻለውን ያህል ይገድላል፣ ያወድማል፤ በለስ ከቀናውም ስልጣን ይቆናጠጣል፡፡
ሌላ የተሻለ ጉልበተኛ ሲመጣ ደግሞ ከነግሳንግስ ሀሳቡ እንዲሁ ደምስሶና ከ “ሀ” አስጀምሮ ወደ ስልጣን ይወጣል፡፡
ኢትዮጵያውያን መኩራራት ያለብን ወንድም ወንድሙን ገድሎ በሚመጣ ጊዜያዊ ስልጣን ሳይሆን ወንድም ለወንድሙ በፍቅርና በሰለጠነ ሽግግር ተሸንፎ በሚደረግ ዘለቄታ ባለው ቅብብል ነው፡፡ ማስፈን ያለብንም ሥርዓት ይሄው ነው፡፡
በምርጫ ካርድ ተሸንፎ “እንኳን ደስ ያለህ” ተባብሎ ትናንት የተጀመረው ላይ ስህተቱ ታርሞ፣ ጎባጣው ቀንቶ፣ እውቀትና እሴት ተጨምሮበት፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ መዓዛ ያለው ሥርዓት የምናወርስበት አዲስ በር መክፈት ሲኖርብን፣ ለሰው የምንተርፍ ለራሳችን የማንሆን፣ እያለን የሌለን ሆነን ዘመናትን ተሻግረናል፡፡
ዓመት የሞላውና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው አውዳሚ ጦርነት መነሻው ከላይ የተጠቀሰው ነው፤ ጉልበትና መሣሪያ! ሲፈጠር ጀምሮ ሴራና ተንኮል፣ የእሱ ስኬት በሌሎች ውድቀት ላይ ብቻ ይሳካል የሚል ክፉ አባዜ የተጠናወተው ሕወሓት የተጨመረለትን እድሜ ለጸጸትና ንሰሓ፣ ብሎም በታሪክ አጋጣሚ ያገኛቸውን ወርቃማ እድሎች ከነሳንካቸው እየጻፈ ትውልድ እንዲማርበት ከማድረግ ይልቅ “የሰሜን ዕዝን መሣሪያ ከነጠኩ የሚነካኝ የለም፣ ሌላውንም ኢትዮጵያዊ በኃይሌ አስገብረዋለሁ” ብሎ በእብሪት ተነሳ፡፡
ውጤቱም ሞት፣ መከራ፣ ስደት፣ የሴቶች መደፈር፣ ሕጻናትና አረጋውያንን በረሀብ መቅጣት ሆነ፡፡
ይህም አልበቃው ብሎ ተንጠራርቶ ድብቅ የእርጅና ስልጣን ጥሙንና ሀገር የማፍረስ ውጥኑን ከግብ ለማድረስ በአማራና አፋር ክልሎች ገብቶ በሰው ልጅ ላይ ይደርሳል ተብሎ የማይታሰብ ሰቆቃን እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ካለፈው ጭካኔው በትንሹ ተምሮ መምጣት ሲገባው ጭራሽ ከአውሬነት ባስ ያለ፣ በግብሩ ሰይጣንን የሚያስንቅ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ከሕጻን እስከ አዋቂ ከነብስ ወከፍ እስከ ከባድ መሣሪያ ተጠቅሞ ይጨፈጭፋል፣ አድባራትንና ገዳማትን ይዘርፋል፣ ገዳማውያኑን ይገድላል፣ መሳጅዶችን ያፈርሳል፣ በውስጥ ያሉ ደረሶችን ያለርህራሔ ይገድላል፣ ዘር የሚተኩ ሴቶችን ይደፍራል፣ በደሃው ብር የተሠሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋመትን ይሰርቃል፣ ያፈርሳል፣ በእይታ ውስጥ የገባን ቤትና እቃ ሁሉ አጥቦ ይጭናል፣ እንስሳትን ከድመት እስከ ግመል ተኩሶ የበቀል ሱሱን ይወጣባቸዋል፣ አዝርዕትን በመጨፍጨፍ በቅጽበት ወደ ጠፍ ምድር ይቀይራል፡፡
በዘረፋና ሌሎችን በማራቆት ራሱን ይመግባል፡፡
ስለሆነም እኛ በአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥር የምንንቀሳቀስ ፓርቲዎች ይህ እኩይ ቡድን በንጹሓን ላይ የሚያደርሰውን ዘግናኝ የሰብዓዊ ቀውስ በጽኑ እያወገዝንና በተባበረ ክንዳችን እንደምንመክተው ቃል እየገባን ለመላ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚከተለው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
1. በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ሊባል በሚችል መልኩ እየተጠራ ያለውን “የክተት አዋጅ” ሙሉ በሙሉ እየደገፍን ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ክትትልና ማሻሻያ እየተደረገለት ያለምንም ሰንጣራ ስህተት ተተግብሮ በአንድ ድንጋይ ሁለት ሳይሆን ብዙ እኩያንን መምቻ ፈጣን ቀስት እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡
2. የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ ይህን ወራሪውን ኃይል ለመመከትና ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ ለመምታት የሚደረግን ዘመቻ ከጦር ኃይሉ ጋር በመሰለፍ በሚችሉት መንገድ ሁሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ፣ አቅማቸው የማይፈቅድላቸው በየአካባቢያቸው በሚደረገው የፀጥታ ጥበቃ እንዲተባበሩ እንጠይቃለን፡፡
3. ባለሀብቶች በዓይነትም ሆነ በገንዝብ ለትጥቅና ስንቅ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
4. መንግሥት ከአንዳንድ ችግሮቹ ጋር እስካሁን ይህን ወራሪ ኃይል ለመመከት ያደረገውን ተጋድሎ እያደነቅን ውስጡን ፈትሾ በአሸባሪው ኃይል ላይ ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡
5. የመረጃ ፍሰቱ ከአጉል የድል ዜናም፣ ሕዝብን በውሸት ከማሸበርም ርቆ ተቋማዊና አግባብ ባለው መንገድ በወቅቱ ለሕዝብ እንዲደርስ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
6. ከዋናው ግንባር በተጓዳኝ ያሉ ጥፋትና ሽብር ግብራቸው በሆኑ አካላት የሚደርሱ ፍጅቶች በዐይነ ቁራኛ እንዲጠበቁ በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡
7. ሁለቱ አሸባሪዎች (ሕወሓትና ሸኔ) እናት ሀገራችንን ለማፍረስ የገቡበትን ያልተቀደሰ ቃልኪዳን እኛ የቁርጥ ቀን ልጆቿ በአንድነት የቃል ኪዳን ገመድ ተሳስረን በድቡሽት ላይ የተሠራ ጊዜያዊ ጎጇቸውን እንደምናፈርሰውና የሀገራችንን ሰላም ወደነበረበት እንደምንመልስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል እንገባለን፡፡
8. ወደፊት በዝርዝር የምናሳውቀው ሆኖ የየፓርቲዎቻችን ሁሉም መዋቅሮች በሚደራጀው የጋራ ግብረ ኃይል ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና ሙሉ ትኩረታችሁን የተደቀነብንን የሕልውና አደጋ መመከት ላይ እንዲሆን እንጠይቃለን ።
9. የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት እናት ሀገራችሁ ባቀረበችላችሁ ጥሪ መሠረት ሀገራችሁን ለመታደግ ለደቂቃም እንኳን እንዳትዘገዩና አፋጣኝ ምላሽ እንድትሰጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
10. የእርዳታ ድርጅቶችና ነብስ አድን ሥራ ላይ የተሠማራችሁ አካላት በጦርነቱ ሰበብ ለተቸገሩ ሁሉ ያለአድልዖ እንድትደርሱ በረሃብና ችጋር በሚጠበሰው ሕዝባችን ስም እንማጸናችኋለን፡፡
11. በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ እሑድ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ
ሊደርግ የታሰበውንና ሚሊዮኖች የሚሳተፉበት ሰልፍ የየፓርቲዎቻችን አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ ልብ ተቀብላችሁ እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ በአንድነት ቆመን ሀገር የምናድንበት ወቅት እንጂ በትንሿ ስኬት የምንሞጋገስብት፣ በተሠራውና ባለፈው ስህተት ጣት የምንቀሳሰርበት ጊዜ አይደለም፡፡
ይልቁንም ከፊታችን የመጣውን ሀገር አፍራሽ ኃይል የምንመክትበትና ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የሰላም አየር እንዲተነፍሱ በጋራ ቆመን መስዋዕትነት የምንከፍልበት ጊዜ እንጂ፡፡
ስለዚህም ተደጋግፈን ሀገራችንን ከገጠማት የውስጥና የውጭ ጠላት ማዳን በእኛ በዜጎቿ ትከሻ ላይ የወደቀ ስለሆነ ወገባችን አስረን፣ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው በጋራ መቆም አለብን እንላለን፡፡
እኛ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትም ከኋላ ቆመን በለው ለማለት ሳይሆን ከፊት ተሰልፈን መስዋዕትነት ለመክፈል የድርሻችን አበርክተን በደምና በአጥንታችን ውዲቷን ሀገራችንን ለመታደግ ቃል በመግባት መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
ክንዳችንን አስተባብረን ጉልበት አምላኪዎችን እንመክታለን፣ የሀገራችንንም ትንሳኤ በደማችን እንጽፋለን፡፡
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ጥቅምት 27 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!