Fana: At a Speed of Life!

በግንቦት ወር 12 ከተሞች ከታዳሽ ሀይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆኑ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተያዘው ዓመት ግንቦት ወር ላይ 12 ከተሞች ከታዳሽ ሀይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን እና ተደራሽነቱ 44 ከመቶ ብቻ ነው።

ከዚህ ውስጥም 33 በመቶ የሚሆኑት ከዋናው የኤሌክትሪክ ቋት አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከታዳሽ ሀይል አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የሀይል ተደራሽነቱን ለማስፋት እና በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኤሌክትሪፊኬሽን መርሀ ግብር ነድፎ እየሰራ ይገኛል።

እየተከናወነ በሚገኘው በዚህ መርሀ ግብርምየመብራት አገልግሎት ያልደረሰባቸው 12 ከተሞች ተመርጠው ከታዳሽ ሀይል አገልግሎቱን እንዲያገኙ ካለፈው አመት ጀምሮ እየተሰራ እንደሚገኝ አገልግሎቱ አስታውቋል።

በሁሉም ክልሎች የሚገኙት እነዚህ 12 የወረዳ ከተሞችም አሁን ላይ ስራቸው እየተገባደደ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

በግንቦት ወር የኤሌትሪክ ሀይል አገልግሎት ከሚያገኙት ከተሞች መካከልም በኦሮሚያ ክልል 3፣ በአማራ ክልል 2፣ በትግራይ ክልል 1 እንዲሁም በደቡብ ክልል ደግሞ 2 ከተሞች ይገኙበታል።

ከዚህ ባለፈም በሌሎቹ ክልሎች አንዳንድ ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

ከተሞቹ እስካሁን የመብራት አግልገሎት ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ ናቸው ያሉት አቶ ሽፈራው፤ በግንቦት ወር ላይ የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ሲያገኙ 70 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

ከተሞቹ ከታዳሽ ሀይል ወይም ከፀሀይ ሀይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ አገልግሎት በአሁኑ ሰአትም በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ ፓናሎችን እየተከለ ይገኛል።

የከተማ የውስጥ ለውስጥ የመስመር ኔትዎርክ ዝርጋታም በሀገር ውስጥ የስራ ተቋራጮች እየተሰሩ መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።

12ቱ ከተሞች ከታዳሽ ሀይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ ለሀይል ማመንጫ ስራው ብቻ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

አቶ ሽፈራው በቀጣይም 25 ከተሞች ወደ ግንባታ እንደሚገቡ ጠቅሰው፥ የንድፍ እና የጨረታ ስራዎች ተሰርተው ለአፍሪካ ልማት ባንክ ተልኳልም ነው ያሉት።

ለእነዚህ ከተሞች 25 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ እንደሚያስፈልግ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፥ የስራ ተቋራጮቹ ከተለዩ በኋላ በ6 ወራት ውስጥ ግንባታዎችን ለማጠናቅቅ ማቀዱን አስታውቋል።

በዙፋን ካሳሁን

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.