የሰላም መከታ ለሆነው መከላከያ ሰራዊት የምንሰስተው ነገር የለም – የምዕራብ ሀረርጌ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም መከታ ለሆነው መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ የምንሰስተው ነገር የለም ሲሉ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን 18 ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን በማውገዝና መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ ዛሬ በጭሮ ከተማ ህዝባዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በጭሮ ስታዲየም በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ የተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች በአሸባሪዎች ህወሓትና ሸኔ እኩይ አላማ ሀገር አትፈርስም ፤በሰብአዊ ድጋፍ ሽፋን ሉአላዊታችንን አሳልፈን አንሰጥም፤ የሚሉና መሰል መፈክሮችን በማሰማት አሸባሪዎችንና ተባባሪዎቻቸውን አውግዘዋል።
ሰልፈኞቹ መንግስት የሀገር ህልውናና ሉአላዊነት ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከልና የንጹሀንን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ላወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኤክራም ጣሃ በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “ኢትዮጵያን በመከፋፈል በጎሳ ፀብ እልቂት እንዲበረክት ሲያደርግ የነበረው የህወሃት ቡድንና አንዳንድ የሀገሪቷን እድገት የማይፈልጉ ያደጉ ሀገራት መሪዎችም ሆኑ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲያሱ እንታገላለን” ብለዋል፡፡
“የሰላማችን መከታ የሆነውን መከላከያ ሃይላችንን ለመደገፍ “የምንሰስተው ነገር የለም፣ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፣ ጁንታው ይደመሰሳል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የጭሮ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ ኡመር በበኩላቸው “በተባበረ የህዝብ ድጋፍ ጁንታውና ተላላኪዎቹን እስከመጨረሻው እንቀብራለን” ብለዋል፡፡
“ሁሉም የሀገራችን ህዝብ ወያኔና ግብረ አበሮቹ የኢትዮጵያ ጠላት መሆናቸውን በአደባባይ ወጥቶ ማውገዙ ይቀጥላል፤ ዘመቻ ሄዶ መከታ መሆኑም ሆነ መከላከያ ሰራዊቱን አስፈላጊ በሚባለው መደገፉም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል ፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!