በኢትዮ ኬንያ ድንበር ማርሳቢት ግዛት ላይ ተጨማሪ የግብይይት ስፋራ ሊከፈት ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ እና የሰዎችን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማሳደግ ከሞያሌ በተጨማሪ በማርሳቢት አካባቢ ተጨማሪ የመገበያያ ስፍራ ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቋን አስታወቀች።
በማርሳቢት ግዛት አስተዳደር ጥያቄ እና ድጋፍ የሚቋቋመው የመገበያያ ስፍራ በሽታዎችን እና በአካባቢው ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር ያችላል ተብሏል።
የኬንያ ድንበር አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኬንደይ ንያዮ፥ በድንበር ከሚዋሰኑ ሀገራት ጋር 26 የመገበያያ ስፍራዎችን ለመክፈት እቅድ መኖሩን በመጥቀስ፥ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኗቸው የድንበር አካባቢዎች እንደሚከፈቱ ገልፀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ሀገራቸው 897 ኪሎ ሜትር ድንበር ከምትዋሰናት ኢትዮጵያ ጋር አንድ የመገበያያ ስፍራ ብቻ እንዳላት እና ይህም ካለው የንግድ አቅም አንፃር በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በተደረሰው የነፃ ንግድ ስምምነት እንደ ማርሳቢት፣ ዋጅራ፣ ማንዴራ እና ቱርካና አይነት አቅም ያላቸው የመገበያያ ስፍራዎችን የማፈላለግ ስራ ሲከናወን እንደነበረ መግለፃቸውን ዘ ስታንዳርድ ዘግቧል።
የኢኮኖሚ፣ የደህነነት እና የመሰረተ ልማት እድገቶች በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አካላትን ገቢ እንደሚያሻሽል እና የንግድ ወጪን እንደሚቀንስ የኬንያ ድንበር አስተዳደር ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision