Fana: At a Speed of Life!

ከአየር ብክለት በጸዳ ሁኔታ ምርታማነትን ለመጨመር የገለባ ማዳበሪያን መጠቀም እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከምርት በኋላ ገለባውን ወደ አፈርነት ቀይሮ ለማዳበሪያነት መጠቀም ምርታማነትን እንደሚጨምር እና አየር ብክለትን ለመከላከል እንደሚያስችል በቻይና የተሰራ ጥናት አመላከተ፡፡

በቻይና ÷ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ገለባውን በማቃጠል የማስወገድ ልምድ በሀገሪቷ አርሶ አደሮች ዘንድ ሲተገበር የኖረ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሞ ÷ ልምዱም የአየር ብክለትን በማባባስ አሉታዊ አስተዋጽዖ ሲያደርስ መቆየቱን አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ ከሆነው የሀገራት የአካባቢ ጥበቃ አተገባበር ጋር ተያይዞም የቻይና መንግስት ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የገለባ አወጋገድ ዘዴ ማስጠናት የግድ ብሎታል፡፡

በዚህም መሰረት በሊያውኒንግ የሚገኘው የኬይኒው የእርሻ ማሣ ተመርጦ ለአካባቢ ተስማሚ በሆነ መንገድ ገለባ የሚወገድበትን ስልት እንዲያጠና እና የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያመላክት ተመረጠ፡፡

ጃኦ ዩጉኦ የተባለው የኬይኒው የእርሻ ማሣ አስተዳዳሪ እንደገለጹት ÷ “ከመንግስት በተሠጠን ኃላፊነት አሥር ዓመት ገደማ በፈጀብን ጥናት ያገኘነው ውጤት “ገለባውን ወደ አፈርነት መቀየር” ወጪ ቀናሽ፣ በማሳ ላይ ለመጠቀም ቀላል እንዲሁም ከአካባቢ ብክለት ነጻ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ወደ አፈርነት የቀየርነውን ገለባ ለማሣችን በማዳበሪያነት በመገልገልም ምርታማነታችንን በ10 በመቶ ማሳደግ ችለናል” ብሏል፡፡

ወደ አፈርነት የተቀየረው ገለባም በጥቅም ላይ ውሎ ማሳው በማዕድናት የዳበረ እንዲሆን ማስቻሉን ጨምረው አስተዳዳሪው መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

በዚህ ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ውይይት የቀጠለ ሲሆን ÷ በመጪዎቹ አስር አመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአለም ሙቀት መጨመርን ለማስቀረት በርካታ ሀገራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓለማየሁ ገረመው

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.