የሀገር ውስጥ ዜና

ለአዋጁ ስኬታማነት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ምሁራን ጠቆሙ

By Alemayehu Geremew

November 09, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ላወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የህግና ፖለቲካ ሣይንስሥ መምህራን ተናገሩ።

የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ኑሩ መኩሪያው ለኢዜአ እንደገለጹት፥ አሸባሪው ህወሓትና ተላላኪዎቹ ሀገር የማፍረስ ተልዕኳቸውን በመደበኛው አሰራርና አደረጃጀት ለማስቆም አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል።

መንግስት የሽብር ቡድኑን ግልጽ የሆነ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ፈጥኖ በመቆጣጠር የህዝብ ሰላምንና የሀገር ደህንነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ ነውም ብለዋል፡፡

እንደ መምህሩ ገለጻ ህወሓት በሀገር ላይ እያካሄደ ያለው ውድመት መንግስትን በሀይል ለመናድ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ልታንሰራራ በማትችልበት ደረጃ አፈራርሶ ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ካለው ፍላጎትም ነው።

የወጣቶች እና ሴቶች እንዲሁም የተለያዩ የሙያ ማህበራትን በመጠቀም የሽብር ቡድኑን የጥፋት ዓላማና ተግባር እንዲሁም በአዋጁ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ላይ መረጃ በመስጠት በህዝብ ውስጥ የጋራ መግባባት መፈጠር አሸባሪውን ለመመከት ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሲቪክስና ሥነዜጋ መምህር አቶ ሙክታር ጠይብ በበኩላቸው ÷ የመንግስት ቁልፍ ተልዕኮ የዜጎችን እና የሀገር ሠላምና ደህንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣት የሽብር ቡድኑ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የደቀነውን ሥጋት ለመቀልበስ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አውስተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር መሀመድ ኢድሪስ፥ ህወሓት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን እያወደመ መሆኑን ገልጸዋል።

በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የመንግስትና የግለሰቦችን ንብረት እየዘረፈ፣ ንጹሀንን በጭካኔ እየገደለና እየጨፈጨፈ የአገርና የዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏልም ነው ያሉት።