Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ቡድን በማይካድራ በፈጸመው ጭፍጨፋ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተጠያቂ የሚያደርግ ዘመቻ ሊጀመር ይገባል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን አመራሮች በማይካድራ በፈጸሙት ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ተጠያቂ የሚያደርግ ዘመቻ ሊጀመር እንደሚገባ ተመለከተ።

ዝክረ ማይካድራ አንደኛ ዓመት የሰማዕታት ዕለት ትናንት ምሽት በጎንደር ከተማ በህሊና ጸሎትና ሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ታስቧል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ጸጋው እዘዘው በወቅቱ እንደተናገሩት ÷ ህወሓት ለአማራ ህዝብ ካለው ጭካኔና ጥላቻ በመነሳት አልሞና አቅዶ ጅምላ የዘር ፍጅት በማይካድራ በአደባባይ ፈፅሟል።

የአሸባሪው ቡድን አመራሮች የፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ በአለም አቀፍ ህግ ጭምር በወንጀል የሚያስጠይቃቸው በመሆኑ ተፈጻሚ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ድምጻችንን እናሰማለን ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባል አቶ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ ታሪክ አስከፊውን የዘር ጭፍጨፋ በማካሄድ እንደ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን የማይካድራ ጅምላ የዘር ጭፈጨፋ አልበቃው ብሎት ወረራ በፈጸመባቸው በሰሜን ጎንደር፣ በአፋር ፣ በወሎና በደቡብ ጎንደር ተመሳሳይ አረመኔያዊ ድርጊት መፈጸሙን ገልጸዋል።

ቡድኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ በፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንዲሆን በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ መረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአሸባሪው የህወሓት አመራሮች የግፍ ጭፍጨፋ መስዋዕት የሆኑ ወገኖች አለም አቀፍ ፍትህ እንዲሰጣቸው በሰማዕታቱ ስም ከተማ አስተዳደሩ አጥብቆ ይጠይቃል ፤ ለተግባራዊነቱም ይሰራል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተወካይ አቶ ዳንኤል ውበት ናቸው፡፡

ቡድኑ በህዝባዊ ትግል ወደ ቆፈረው ጉድጓድ ገብቶ በአጭር ጊዜ እንዲቀበር ለማድረግ የህልውና ዘመቻውና ሀገር የማዳን ተጋድሎው በአንድነትና በህብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዝክረ ሰማዕታቱ መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓቱ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ አጥኝ ቡድን አስተባባሪ አቶ ጌታ አስራደ ÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈጸመው ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ 1ሺ 644 ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሰማዕት ከሆኑት የአማራ ተወላጆች መካከልም 1ሺህ 563 በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ÷ 81 ሰዎች ደግሞ የእድሜ ልክ አካል ጉዳተኛ በመሆን በህይወት መትረፋቸውን አጥኚው ቡድን በአካባቢው ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን አስታውቀዋል።

በማይካድራው በተፈጸመው ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ፈጻሚዎች በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ክስ ሊመሰረትባቸው የሚችሉ ተጨባጭ የምርመራ ሰነዶችን ቡድኑ በሚገባ ማደራጀቱንም አብራርተዋል።

የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች የፈጸሙትን ወንጀል ለአለም አቀፍ ህብረተሰብ፣ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን ጭምር ለማጋለጥ የጥናት ቡድኑ አለም አቀፍ መድረኮችን ለመጥራት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በዝክረ ሰማዕታቱ መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.