የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከህልውና ዘመቻው በተጓዳኝ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡
በፌዴራል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ከተቋቋሙት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ የሆነው የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፈው ዓመት ተመርቆ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን እስካሁን ለ1 ሺህ 300 ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመረ ሲሆን ይህም የክልሉን ብሎም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በወቅታዊ ችግር ምክንያት እንዳይጎዳ ያግዛል ተብሏል።
በፓርኩ የማምረቻ ሼድ ወስደው በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ሆፕ ሉን አፓረን ኢትዮጵያ ልብሶችን አምርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ለውጭ ገበያ አቅርቧል፡፡
በሆፕ ሉን አፓረን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰው ሃብት ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡልቲ ሙህየ ድርጅቱ ያመረታቸውን 75 ሺህ ያህል አልባሳት ዛሬ ወደ አሜሪካ እንደሚልክ እና ከ570 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ፓርኩ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጥሩየ ቁሜ ናቸው፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ፋይዳው የጎላ ይሆናል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጇ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የክህሎት ሽግግር እና የውጭ ምንዛሬ ችግሮችን መቅረፍ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ተቀዳሚ ዓላማዎች ናቸዉ ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል::
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!