Fana: At a Speed of Life!

ሽንፈት ታሪካችን አይደለም – ጠ/ሚ ዐቢይ

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሽንፈት ታሪካችን አይደለም ሲሉ ገለጹ።

አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ የውይይት መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት “የሕልውና ጥሪ እና አገርን የማዳን ርብርብ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ሽንፈት ታሪካችን አይደለም” ኢትዮጵያውያን ወደ ሰላም መመለስ ይፈልጋሉ፤ ይህንንም ግብ አድርገን እንሠራለን” ብለዋል።

ባልተገባ ሁኔታ የወገንን መረጃ ጠላት እንዲያገኝ ማድረግ አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ያለንበት ጦርነት መሠረታዊ ጦርነት ጥይቱ ሳይሆን የሀሰት ወሬው ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም ጠላት ቢዋሽ የሚጠይቀው አካልም ሆነ እንዳይዋሽ የሚከለክለው የሞራል ቁመና የሌለው በመሆኑ እንዳሻው መዋሸትና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንደሚያሰራጭም አንስተዋል።

ይሁንና መንግሥት በመሰል ሁኔታ ውሸትን ማሰራጨትና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የመንዛት ፍላጎትም ሆነ የሞራል ፍቃድ የለውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ ጥንታዊ ብትሆንም ባለፉት 30 አመታት ወንድማማችነትን የሚያላላ ብዙ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያን አለት ላይ የመገንባት ታላቅ የአገር ግንባታ ሥራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ሁሉ በፅናት አልፋ ቀና ብላ የድል ታሪኳን ለሌሎችም የምታስተምር እንድትሆን በርካታ መስዋዕትነት እየከፈልን እንገኛለንም ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን እኔ አንበርክኬ መግዛት አለብኝ ፤ መግዛት ካልቻኩም አፈራርሻት በፍርስራሿ ላይ እኖራለሁ ብሎ ያሰበ ኃይል የከፈተባት የሕልውና ጦርነት ውስጥ ትገኛለች ብለዋል።

በዚህ የሕልውና ዘመቻ ላይም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመጠበቅ በፍፁም አርበኝነት ስሜት ከዳር ዳር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት ንቅናቄ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፈተናው ለሕዝቦች የጋራ እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ያነሱት ዶክተር ቢቂላ፥ በአድዋ ወቅት ከነበረው ንቅናቄ ባልተናነሰ መልኩ ሕዝቡ በአርበኝነት ከዳር ዳር መነቃነቁንም አውስተዋል።

የሕዝቦች አርበኝነት ንቅናቄ አገርን ለማዳን መዝመት፣ መጠበቅ እና አገርን መደገፍ የሚል መሰረታዊ መርህ እንዳለውም አብራርተዋል።

በዚህ ደግሞ ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳለ ማሳየት ተችሏል ማለታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.