ኮሮናቫይረስ

የጀርመኗ ሄሰን ግዛት ነዋሪዎች ኮሮና ቢጠፋም መጨባበጥ የለም ብለዋል

By ዮሐንስ ደርበው

November 11, 2021

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመናውያን ኮሮና ቫይረስ ቢጠፋ እንኳን መጨባበጥና መተቃቀፍ እንደሚያቆሙ ለራሳቸው ቃል መግባታቸውን ገለፁ።

በጀርመን ሄሰን ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ብዙዎች ወረርሽኙ ካለቀ በኋላም ጓደኞቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ማቀፍ ለማቆም መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

በግዛቷ የጤና መድን ሰጪው ኤ ኦ ኬ ያደረገው ጥናት እንዳመላከተው÷ የግዛቷ ነዋሪዎች ከድህረ ኮሮና በኋላ ቀድሞ ወደነበረው የሰላምታ አሰጣጥም ሆነ ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደማይመለሱ አመላክቷል።

በጥናቱ መሰረት 1/3 የሚሆኑት የግዛቷ ነዋሪዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ከማቀፍ እንቆጠባለን ብለዋል።

ከግዛቷ ነዋሪዎች በተሰበሰበው አስተያየት መሰረት 39 በመቶ የሚሆኑት ከማንም ጋር መጨባበጥን ለማቆም ለራሳቸው ቃል እንደገቡ እና 64 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ብቻ መጨባበጥ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም 23 በመቶ የሚሆኑት ከወረርሽኙ በኋላ በሕይወታቸው ውስጥ ሰዎችን ወደ ቤታቸው መጋበዝ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት የኮቪድ-19 ወረረሽን በአብዛኛው ከሚተላለፍባቸዉ መንገዶች ዋነኞቹ የፍቅር መግለጫዎች እና የሰዎች የዕለት ከዕለት መስተጋብር እንደምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

ምንም እንኳን ጠንከር ያሉ ህጎች ቢተገበሩም በጀርመን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት ከፍ ማለቱን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

በሚኪያስ አየለ