Fana: At a Speed of Life!

መላው ሕዝብ የተደረገለትን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ባደረገው የተቀናጀ እንቅስቃሴ በተለያዩ ግንባሮች አኩሪ ድል ተመዝግቧል – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተደረገለትን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበልና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው እንቅስቃሴ በተለያዩ ግንባሮች አኩሪ ድል እንዲመዘገብ ማድረጉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታወቀ።

የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለውና በበላይነት የሚመራው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ቁ.2 እንዳሰተወቀው ፥ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሀገራዊ ሁኔታና የአዋጁን አፈጻጸም ሁኔታ ትናንት ማምሻውን የገመገመ ሲሆን፣ ለኅብረተሰቡ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ፣ የአዋጁን አፈጻጸምና ወታደራዊ እርምጃዎች በመገምገም የተለያዩ ድሎች መመዝገባቸውን አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት ፥ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ ፥ የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልሎች ሕዝብ የተደረገላቸውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ወደሁሉም ግንባሮች መክተቱንና ሌሎችም በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል።

በባቲ- አሳጊታ ግንባር የጥፋት ኃይሉ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ከ20 ያላነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን አድርጓል።

ጀግኖቹ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀትና በስሥሮቹ የአየር ኃይል አባላት በመታገዝ፣ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሣራ በማድረስ፣ ሁሉንም የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አክሽፈው ወራሪ ሽንፈትን እንዲከናነብ አድርገውታል።

የጠላት ኃይል ሚሌን ለመያዝ የነበረውንም ፍላጎት የሕልም እንጀራ አድርገውበታል ብሏል።

በትግራይ እና አፋር ክልሎች ወሰን ላይ ቢሶበር አካባቢ ጁንታው ትናንት የከፈተውን አዲስ የማጥቃት ሙከራ፣ አንበሶቹ የአፋር ሚሊሻና ልዩ ኃይል የጠላትን አከርካሪ ሰብረው በዚህ ግንባር የመጣውን ጠላት አሳፍረው የመለሱይ መሆኑንም ዕዙ አስታውቋል።

በወረኢሉ ግንባር እንዲሁ ለመስፋፋት አስቦ የተንቀሳቀሰው የጠላት ኃይል፣ በደቡብ ወሎ ሚሊሻና በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተመትቶ የመከነበት መሆኑን ነው የገለጸው።

በተጨማሪም በአቀስታ ግንባር ለመንቀሳቀስ አስቦ የነበረው የጁንታ ኃይል በአዊ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በምሥራቅ ጎጃምና በደቡብ ወሎ ሚሊሻ ተመትቶ ወደኋላ ለማፈግፈግ መገደዱ ተገልጿል።

በከሚሴ ግንባር ያሉት የመከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሞ ብሔረሰብና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ሚሊሻዎችም ባለፉት አምስት ቀናት ባደረጉት ተጋድሎ፣ ወረራውን በመቀልበስ፣ ወደ ፀረ- ማጥቃት እንቅስቃሴ ተሸጋግረዋል።

በማይጸብሪ ግንባርም የጥፋት ኃይሉ ተደጋጋሚ ፀረ- ማጥቃት ቢያደርግም እንቅስቃሴው መክሸፉን ነው የዕዙ መግለጫ ያመለከተው።

በአጠቃላይ በአማራና በአፋር ክልሎች የክተት አዋጁን ተከትሎ በጠላት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ አመርቂ ሆኖ መገኘቱን ገልጾ፥ ለዚህ መሠረቱ የሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ መነሣሣትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የፈጠረው ንቅናቄ መሆኑ ተረጋግጧል።

በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮጉድሩ እና በምሥራቅ ወለጋ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ፣ ሰላማዊውን ሕዝብ በመግደልና ንብረት በመዝረፍ፣ የጁንታውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ የነበረውን አሸባሪውን የሸኔ ቡድን በመደምሰስ ግብርአበሮቹን በቁጥጥር ሥር የደረገ ሲሆን፣ ይህን ከፍተኛ ድል ለመጎናጸፍ የተቻለውም የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ የጋራ ጥምረት መሆኑን ዕዙ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.