Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተካሄደ ያለውን ሴራ ለማክሸፍ ጠንክረን እንሰራለን- የጋምቤላ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን አሸባሪው የህወሓት ቡድንና የተላላኪዎቹን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ ጠንክረው እንደሚሰሩ የጋምቤላ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ገለጹ፡፡

ከክልሉ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የአመራር አካላት በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ሲያካሄዱ የቆዩትን ውይይት መግለጫ በማውጣት አጠናቀዋል።

ተሳታፊዎቹ በመግለጫቸው÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተላላኪዎቹ በንጹሐን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና የመሰረተ ልማት አውታሮች ጥፋት ለማስቆም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ርብረብ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ጊዜው ያለፈበትን የመጨዋቻ ካርድ በመያዝ በአሻንጉሊቶቻቸው አማካኝነት እየፈጠሩት ያለውን ጫና አጥብቀው እንደሚቃወሙም አስታውቀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በጋምቤላ ክልል በኑዌር፣ አኝዋሃና ማጀንግ ላይ ብሔር ተኮር ጥቃትና ዘረፋ ሲፈጽም እንደነበር አስታውሰው ÷ አሁንም ከተላላኪዎቹ ጋር በመሆን የቀድሞውን ድርጊት ለመድገም የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አምርረው እንደሚታገሉ ገልጸዋል።

በየግንባሩ እየተዋደቀ ካለው የመከላከያ ሰራዊት፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣትም ቃል ገብተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በተንኮል ተወልዶ በውሸት ያደገ የኢትዮጵያና ህዝቦቿ ቀንደኛ ጠላት ነው ብለዋል።

የጥፋት ቡድኑ እየቃጣ ያለውን ሀገር የማፈረስ እኩይ ተግባር ለመቀልበስ ሁሉም የህልውና ዘመቻው አካል ሊሆን እንደሚገባ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ ያሳሰቡት።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከ220 በላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና አመራሮች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.