የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትወርክ ለተፈናቃዮች የ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

By ዮሐንስ ደርበው

November 11, 2021

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ድርጅት በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፉ ካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሸዋ ሰላምና ልማት ማህበር በኩል ለወሎ ተፈናቃዮች የተገኘ መሆኑን የሸዋ ሰላምና ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቼው ተናግረዋል።

ማህበሩ ተፈናቃዮች ያሉባቸውን ችግሮች ቀድሞ በማየት ደብረ ብርሃን ከተማ በአራት ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሩዝ፣ ብርድ ልብስ፣ የመመገቢያና ማብሰያ ቁሳቁስ ፣ ዘይትና ፍራሽ ድርጅቱ ገዝቶ ማስረከቡንም ነው የተናገሩት።

ሌሎች ድርጅቶችም በዚህ መልኩ ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ድርጅት ተወካይ አቶ ከበደ ኃይለማርያም እንደገለፁት፥ ተፈናቃዮቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳዛኝና ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልግ በመሆኑ በካናዳና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል።

ከወሎ ኡርጌሳና መርሳ ከተሞች የመጡና በደብረ ብርሃን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኙት ተፈናቃዮች እንደገለፁት፥ የነበረባቸው ቁሳቁስ እጥረት አሁን እየተቀረፈ ቢሆንም የሚደረገው ድጋፍ በቂ አይደለም ማለታቸውን ከሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘና መረጃ ያመላክታል፡፡