Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እያደረገ ያለው ሙከራ አይሳካም – መንግስት ኮሙኒኬሽን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በህዝብ የተመረጠን መንግስት በመገልበጥ አገሪቱን መንግስት አልባ እና የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የሽብር ድርጊት መፈጸሙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዲኤታዋ የሽብር ቡድኑ ድርጊት በሃገር ወዳድ ህዝቦች ትግል እንደሚከሽፍና አገር የማፍረስ ሙከራው እንደማይሳካም ተናግረዋል።

በአልጀዚራ ቴሌቪዝን ቢላሁዱድ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በመጣል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አላማ አድርጎ ባለፈው አመት ጥቅምት 24 ቀን ሰሜን እዝን በመውጋት ጦርነት ካወጀ ጀምሮ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ግፍ ተፈጽሟል፡፡

ይህንን ተከትሎም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ በሰራው ስራ የአሸባሪውን ቡድን የሽብር ኢላማዎች ቀልብሶ ህግ የማስከበር ስራ መስራቱን አስታውሰዋል።

ከዛ በኋላም የሰብል ወቅት በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ወደ ተለመደ ስራው እንዲገባ እፎይታ ለመስጠት በሚል የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ከክልሉ በወጣበት ወቅት አሸባሪ ቡድኑ እንደገና ሀይሉን በማደራጀት በአማራ እና በአፋር ክልል ወረራ መፈጸሙን አስረድተዋል።

በሁለቱ ክልሎች ባደረገው ወረራም ንጹሀን ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የህይወት እና የንብረት ውድመት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል ሚኒስትር ዲኤታዋ፡፡

መንግስት በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች ጦርነቱ ጉዳት ባደረሰባቸው ቦታዎች አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆንም አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ተጎጅዎች እርዳታ እንዳልተደረገ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት በትግራይ ህዝብ ስም የራሱን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህ ማሳያ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ከተማ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ መሆኑ እየታወቀ አዲስ አበባ ዙሪያ ደርሻለሁ፤ ከተማውን ልቆጣጠር ነው በማለት የነዛው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የብዙ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቦ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እውነታውን ለመዘገብ ከፈለጉ ቦታው ድረስ በመምጣት ሽፋን መስጠት እንደሚችሉ እና ለዚህም መንግስት ሁሉን አቀፍ ትብብር እንደሚያደርግላቸውም ጠቁመዋል፡፡

ጦርነቱ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ አላስተጓጎለም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ጦርነቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና የሰው ሃይል ላይ ጉዳት ቢያደርስም፥ በግድቡ ግንባታ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማይፈጥር ገልጸዋል።

ግድቡም በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ በመጥቀስ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ያለውን አለመግባባት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንደሚፈታ ጽኑ እምነት አለኝ ነው ያሉት፡፡

 

 

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.