በድሬዳዋ አስተዳደር የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር ከሰኞ ህዳር ጀምሮ ለአስር ቀናት የሚቆይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ዘመቻውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ÷ በዘመቻው በአስተዳደሩ ነዋሪ ለሆኑ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎችን ለመከተብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
በድሬዳዋ ከመጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እየተሰጡ ቢሆንም እስካሁን ክትባቱን የወሰዱት ሠዎች 39 ሺህ 544 ብቻ በመሆናቸውና ይህም የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ባለመሆኑ ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን በዘመቻ መልክ ለመስጠት ታቅዶ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ወይዘሮ ለምለም አመልክተዋል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር ሲሰጡ ከነበሩት አስትራዜኒካና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በተጨማሪ ሲኖፋርምና ፋይዘር የተባሉ ተጨማሪ የኮቪድ 19 መከላከያ የክትባት አይነቶች የሚሰጡ ሲሆን ÷ ክትባቱን መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በኢንደስትሪዎችና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና በማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩና እንዲሁም ሌሎች ክትባቱን ማግኘት ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከህዳር 6 ጀምሮ እስከ 15 ድረስ ክትባቱ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአሁን ወቅት በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየተሰራጨ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ድሬዳዋ አንዷ መሆኗን፣ ባለፉት ሁለት ወራት የታየው የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ እንደሆነ፣ በነዚህ ሁለት ወራት ብቻ በአስተዳደሩ የ54 ሰዎች ህይወት በኮቪድ ሳቢያ ያለፈ፣ ለፅኑ ህመምና ሞት ተጋላጭ የሚሆኑት ህሙማን በአብዛኛው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ያልወሰዱ ስለመሆናቸው ወ/ሮ ለምለም ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ ለአስር ቀናት ቢሰጠው የክትባት ዘመቻ ክትባቱን በመውሰድ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳር አስከ ትላንት ድረስ ለ57ሺህ 324 ሠዎች ምርመራ ተደርጎ ከ7 ሺህ 700 በሚበልጡት ላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው እስካሁንም በኮቪድ 19 ሳቢያ የ137 ሠዎች ህይወት ማለፉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተሾመ ኃይሉ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!