የሀገር ውስጥ ዜና

የክህደት ጦርነቱን ከመከላከያ ጎን በመቆም እንደሚመክቱ የሸካ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ

By Alemayehu Geremew

November 12, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጁንታው አገርን ለማፈራረስ የከፈተውን የክህደት ጦርነት ለመቀልበስ ከመከላከያ ጎን ሆነው እንደሚመክቱ የሸካ ዞን የማሻ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ነዋሪዎቹ የውጪ መንግስታት እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱም ጠይቀዋል።

የሸካ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ማሞ ÷ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር አገራችን የተያያዘችውን የዕድገትና የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ የማፈራረስ ዓላማ ይዞ የተነሳውን ወራሪ ጁንታ ለመመከት ህዝቡ ከዳር እስከዳር እየተመመ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ ህዝብ ከመከላከያ ጎን በመሆን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀው አገሪቱ የገጠማትን ፈተና እስክምትወጣ ድረስ ህዝቡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግና ለመዝመት ዝግጁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ሳያውቁም ሆነ አውቀው ወራሪውን የሚደግፉትን በማጋለጥም አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

በሸካ ዞን የማሻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ፍስሀ በበኩላቸው÷ የድጋፍ ሠልፉ ከውጪ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሚሰራውን ጁንታ ለመመከት ያለመና ህዝቡ ለመከላከያ ያለውን አለኝታነትን ለመግለፅ አልሞ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህወሓት ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ህዝቦቿ እያሉ አገራችንን ሊያፈርስ አይችልም ያሉት ከንቲባ የጁንታው ግብኣት መሬት እስከሚፈጸም ድረስ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ነዋሪው ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹ የክህደት ጦርነት ለመቀልበስ በፅናት ተሰልፈናል፣ ታላቁ የለውጥ ጉዟችን በውስጥና በወጪ ሴረኞች አይደናቀፍም፣ የህልውና ዘመቻውን በድል ለመቋጨት በዓላማ ፅናትና በሁለንተናዊ ህዝባዊ ዝግጁነት ከመከላከያ ጎን እንደሚሰለፉና በመዝመትም የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ መግለጻቸውን የዞኑን ኮሙኒኬሽን ጠቅሶ የዘገበው ኢፕድ ነው።